ምዕራፍ 137
1በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን።
2በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን።
3የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም። የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን።
4የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?
5ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ።
6ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ።
7አቤቱ፥ በኢየሩሳሌም ቀን የኤዶምን ልጆች አስብ። እስከ መሠረትዋ ድረስ አፍርሱ አፍርሱ ያሉአትን።
8አንቺ ወራዳ የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ስለ ተበቀልሽን የሚበቀልሽ የተመሰገነ ነው።
9ሕፃናቶችሽን ይዞ በዓለት ላይ የሚፈጠፍጣቸው የተመሰገነ ነው።