ምዕራፍ 138
1አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ የአፌን ነገር ሰምተኸኛልና፤ በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ።
2ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህ ስምህንም አመሰግናለሁ፥ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና።
3በጠራሁህ ቀን በፍጥነት አድምጠኝ፤ ነፍሴን በኃይልህ በብዙ አጸናሃት።
4አቤቱ፥ የምድር ነገሥታት ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ የአፍህን ቃል ሁሉ ሰምተዋልና።
5በእግዚአብሔርም መንገድ ይዘምራሉ፤ የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና።
6እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል።
7በመከራ መካከል እንኳ ብሄድ፥ አንተ ሕያው ታደርገኛለህ፤ በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጆቼን ትዘረጋለህ፥ ቀኝህም ታድነኛለች።
8እግዚአብሔር ብድራትን ይመልስልኛል፤ አቤቱ፥ ምሕረትህ ለዘላለም ነው፤ አቤቱ፥ የእጅህን ሥራ ቸል አትበል።