English

ምዕራፍ 140

1ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።
2አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ፤ ቀኑን ሁሉ ለሰልፍ ይከማቻሉ።
3ምላሳቸውን እንደ እባብ ሳሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእፉኝት መርዝ ነው።
4አቤቱ፥ ከኃጢአተኞች እጅ ጠብቀኝ፥ እርምጃዬንም ሊያሰናክሉ ከመከሩ ከዓመፀኞች አድነኝ።
5ትዕቢተኞች ወጥመድን ሰወሩብኝ፥ ለእግሮቼም የወጥመድ ገመድን ዘረጉ፤ በመንገድ ዕንቅፋትን አኖሩ።
6እግዚአብሔርንም። አንተ አምላኬ ነህ፤ የልመናዬን ቃል፥ አቤቱ፥ አድምጥ አልሁት።
7አቤቱ፥ ጌታዬ፥ የመድኃኒቴ ጕልበት፥ በሰልፍ ቀን ራሴን ሸፈንህ።
8አቤቱ፥ ከምኞቴ የተነሣ ለኃጢአተኞች አትስጠኝ፤ በላዬ ተማከሩ፤ እንዳይጓደዱ አትተወኝ።
9የሚከብቡኝን ራስ የከንፈራቸው ክፋት ይክደናቸው።
10የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፤ እንዳይነሡም ወደ እሳትና ወደ ማዕበል ይጣሉ።
11ተናጋሪ ሰው በምድር ውስጥ አይጸናም፤ ዓመፀኛን ሰው ክፋት ለጥፋት ይፈልገዋል።
12እግዚአብሔር ለድሀ ዳኝነትን ለችግረኛም ፍርድን እንዲያደርግ አወቅሁ።
13ጻድቃንም በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፤ ቀኖችም በፊትህ ይኖራሉ።