ምዕራፍ 139
1አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም።
2አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ።
3ፍለጋዬንና ዕረፍቴን አንተ መረመርህ፤ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥
4የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ።
5አቤቱ፥ አንተ እነሆ የቀድሞውንና የኋላውን አወቅህ፤ አንተ ፈጠርኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ።
6እውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች፤ በረታች፥ ወደ እርስዋም ለመድረስ አልችልም።
7ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?
8ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ።
9እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥
10በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።
11በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች፤
12ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው።
13አቤቱ፥ አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል።
14ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።
15እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም።
16ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።
17አቤቱ፥ አሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደ ምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቍጥራቸውም እንደ ምን በዛ!
18ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፤ ተነሣሁም፥ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ።
19አቤቱ፥ አንተ ኃጢአተኞችን የምትገድል ከሆንህስ፥ የደም ሰዎች ሆይ፥ ከእኔ ፈቀቅ በሉ።
20በክፋት ይናገሩብሃልና፤ ጠላቶችህም በከንቱ ያምፁብሃል።
21አቤቱ፥ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? ስለ ጠላቶችህም አልተሰቀቅሁምን?
22ፍጹም ጥል ጠላኋቸው፥ ጠላቶችም ሆኑኝ።
23አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፍተነኝ መንገዴንም እወቅ፤
24በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፤ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ።