ምዕራፍ 142
1በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፤ በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ለመንሁ።
2ልመናዬን በፊቱ አፈስሳለሁ፤ መከራዬንም በፊቴ እናገራለሁ።
3ነፍሴ በውስጤ ባለቀች ጊዜ መንገዴን አወቅሁ፤ በምሄድባት በዚያች መንገድ ወጥመድን ሰወሩብኝ።
4ወደ ቀኝ ተመለከትሁ አየሁም፥ የሚያውቀኝም አጣሁ፤ መሸሸጊያም የለኝም፥ ስለ ነፍሴም የሚመራመር የለም።
5አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ። አንተ ተስፋዬ ነህ፥ በሕያዋንም ምድር አንተ እድል ፈንታዬ ነህ አልሁ።
6እጅግ ተቸግሬአለሁና ወደ ልመናዬ አድምጥ፤ በርትተውብኛልና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ።
7አቤቱ፥ ስምህን አመሰግን ዘንድ፤ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት፤ ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ።