English

ምዕራፍ 143

1አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፤ በእውነትህ ልመናዬን አድምጥ፥ በጽድቅህም መልስልኝ።
2ሕያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባሪያህ ጋር ወደ ፍርድ አትግባ።
3ጠላትህ ነፍሴን አሳድዶአታል፥ ሕይወቴንም በምድር ውስጥ አጐስቍሎአታል፤ ቀድሞ እንደ ሞተ ሰው በጨለማ አኑሮኛል።
4ነፍሴ በውስጤ አለቀችብኝ፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ።
5የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፥ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ።
6እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች።
7አቤቱ፥ ፈጥነህ ስማኝ፤ ነፍሴ አልቃለች፤ ፊትህን ከኔ አትመልስ፥ ወደ ጕድጓድም እንደሚወርዱ አልሁን።
8አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ።
9አቤቱ፥ ወደ አንተ ተማፅኛለሁና ከጠላቶቼ አድነኝ።
10አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፤ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ።
11አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤ በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት።
12በምሕረትህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው፥ እኔ ባሪያህ ነኝና ነፍሴን የሚያስጨንቁአትን ሁሉ አጥፋቸው።