English

ምዕራፍ 145

1አምላኬ ንጉሤ ሆይ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፥ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም እባርካለሁ።
2በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ።
3እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም።
4ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፥ ኃይልህንም ያወራሉ።
5የቅድስናህን ግርማ ክብር ይናገራሉ፥ ተኣምራትህንም ይነጋገራሉ።
6የግርማህንም ኃይል ይናገራሉ፥ ታላቅነትህንም ይነጋገራሉ፥ ብርታትህንም ይነጋገራሉ።
7የቸርነትህን ብዛት መታሰብ ያወጣሉ፥ በጽድቅህም ሐሤትን ያደርጋሉ።
8እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው፥ ከቍጣ የራቀ፥ ምሕረቱም ብዙ ነው፤
9እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው። ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው።
10አቤቱ፥ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፥ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል።
11የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፥ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፥
12ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ
13መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው።
14እግዚአብሔር በቃሎቹ የታመነ ነው፥ በሥራውም ሁሉ ጻድቅ ነው፤ እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፥ የወደቁትንም ያነሣቸዋል።
15የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ።
16አንተ እጅህን ትከፍታለህ፥ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ።
17እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።
18እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።
19ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፥ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም።
20እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል።
21አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ሥጋም ሁሉ ለዘላለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ።