ምዕራፍ 144
1እግዚአብሔር አምላኬ ይባረክ፥ ለእጆቼ ሰልፍን፥ ለጣቶቼም ዘመቻን የሚያስተምር፤
2መሓሪዬና መሸሸጊያዬ፥ መጠጊያዬና መድኃኒቴ፤ ረዳቴና መታመኛዬም፤ ሕዝቤንም ከእኔ በታች የሚያስገዛልኝ።
3አቤቱ፥ እርሱን ታውቀው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ታስብለት ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?
4ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል፤ ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል።
5አቤቱ፥ ሰማዮችህን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው ውረድም፤ ተራሮችን ዳስሳቸው ይጢሱም።
6መብረቆችህን ብልጭ አድርጋቸው በትናቸውም፤ ፍላጾችህን ላካቸው አስደንግጣቸውም።
7-
8እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም ከብዙ ውኆች፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ።
9አቤቱ፥ አዲስ ቅኔ እቀኛልሃለሁ፤ አሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልሃለሁ።
10ለነገሥታት መድኃኒትን የሚሰጥ፥ ባሪያውን ዳዊትን ከክፉ ሰይፍ የሚያድነው እርሱ ነው።
11አድነኝ፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸውም የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ።
12ልጆቻቸው በጕልማስነታቸው እንደ አዲስ አትክልት የሆኑ፥ ሴቶች ልጆቻቸውም እንደ እልፍኝ ያማሩና ያጌጡ፤
13ዕቃ ቤቶቻቸውም የተሞሉ በየዓይነቱ ዕቃ የሚሰጡ፥ በጎቻቸውም ብዙ የሚወልዱ፥ በማሰማርያቸውም የሚበዙ፥
14ላሞቻቸውም የሚሰቡ፤ ቅጥራቸውም መፍረሻና መውጫ የሌለው፥ በአደባባዮቻቸውም ዋይታ የሌለ፤
15እንደዚህ የሚሆን ሕዝብ የተመሰገነ ነው፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው።