ምዕራፍ 38
1አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ።
2ፍላጾችህ ወግተውኛልና፥ እጅህንም አክብደህብኛልና።
3ከቍጣህ የተነሣ ለሥጋዬ ጤና የለውም፤ ከኃጢአቴም የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም።
4ኃጢአቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና።
5ከስንፍናዬ የተነሣ ቍስሌ ሸተተ በሰበሰም፤
6እጅግ ጐሰቈልሁ ተዋረድሁም፥ ሁልጊዜም በትካዜ እመላለሳለሁ።
7ነፍሴ ስድብን ተሞልታለችና፥ ለሥጋዬም ጤና የላትምና።
8ታመምሁ፤ እጅግም ተቸገርሁ፥ ከልቤ ውዝዋዜም የተነሣ ጮኽሁ።
9አቤቱ፥ ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው፥ ጭንቀቴም ከአንተ አይሰወርም።
10ልቤ ደነገጠብኝ፥ ኃይሌም ተወችኝ፥ የዓይኖቼም ብርሃን ፈዘዘ።
11ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ከቍስሌ ገለል ብለው ቆሙ፥ ዘመዶቼም ርቀው ቆሙ።
12ነፍሴንም የሚሹአት በረቱብኝ፥ መከራዬንም የሚፈልጉ ከንቱን ተናገሩ፥ ሁልጊዜም በሽንገላ ይመክራሉ።
13እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቆሮ አፉንም እንደማይከፍት ዲዳ ሆንሁ።
14እንደማይሰማ ሰው በአፉም ተግሣጽ እንደሌለው ሰው ሆንሁ።
15አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና፤ አቤቱ አምላኬ፥ አንተ ትሰማኛለህ።
16ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ እንዳይላቸው ብያለሁና፥ እግሮቼም ቢሰናከሉ ራሳቸውን በእኔ ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።
17እኔስ ወደ ማንከስ ቀርቤአለሁና፥ ቍስሌም ሁልጊዜም በፊቴ ነውና።
18በደሌን እናገራለሁና፥ ስለ ኃጢአቴም እተክዛለሁ።
19ጠላቶቼ ሕያዋን ናቸው ይበረቱብኝማል፥ በጠማማነትም የሚጠሉኝ በዙ።
20ጽድቅን ስለ ተከተልሁ፥ በበጎ ፋንታ ክፉን የሚመልሱልኝ ይጠሉኛል።
21አቤቱ፥ አንተ አትጣለኝ፤ አምላኬ፥ ከኔ አትራቅ።
22አቤቱ መድኃኒቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።