English

ምዕራፍ 39

1በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ።
2ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ቍስሌም ታደሰብኝ።
3ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ፤ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ።
4አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ።
5እነሆ፥ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው፤ አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው።
6በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጣላ ይመላለሳል፤ ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም።
7አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው።
8ከኃጢአቴ ሁሉ አድነኝ፥ ለሰነፎችም ስድብ አታድርገኝ።
9አንተ ሠርተኸኛልና ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም።
10መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ፥ ከእጅህ ብርታት የተነሣ አልቄአለሁና።
11በተግሣጽህ ስለ ኃጢአቱ ሰውን ዘለፍኸው፥ ነፍሱም እንደ ሸረሪት ድር ታልቃለች፤ በእውነት ሰው ሁሉ ከንቱ ነው።
12አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ፤ እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፥ እንደ አባቶችም እንግዳ ነኝና።
13ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ።