ምዕራፍ 50
1የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ከፀሓይም መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ምድርን ጠራት።
2ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል።
3አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊት ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ።
4በላይ ያለውን ሰማይን ምድርንም በሕዝቡ ለመፍረድ ይጠራል፤
5ከእርሱ ጋር ለመሥዋዕት ኪዳን የቆሙትን ቅዱሳኑን ሰብስቡለት።
6ሰማያት ጽድቁን ይናገራሉ፥ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና።
7ሕዝቤ፥ ስማኝ፥ ልንገርህ፤ እስራኤልም፥ ስማኝ፥ ልመስክርብህ፤ አምላክስ እኔ አምላክህ ነኝ።
8ስለ ቍርባንህ የምዘልፍህ አይደለሁም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህ ሁልጊዜ በፊቴ ነው።
9ከቤትህ ፍሪዳን ከመንጋህም አውራ ፍየልን አልወስድም፤
10የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና።
11የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፥ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው።
12ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና።
13የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን?
14ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤
15በመከራ ቀን ጥራኝ፥ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ።
16ኃጢአተኛውን ግን እግዚአብሔር አለው። ለምን አንተ ሕጌን ትናገራለህ? ኪዳኔንም በአፍህ ለምን ትወስዳለህ?
17አንተስ ተግሣጼን ጠላህ፥ ቃሎቼንም ወደ ኋላህ ጣልህ።
18ሌባውን ባየህ ጊዜ ከእርሱ ጋር ትሮጥ ነበር እድል ፈንታህንም ከአመንዝሮች ጋር አደረግህ።
19አፍህ ክፋትን አበዛ፥ አንደበትህም ሽንገላን ተበተበ።
20ተቀምጠህ ወንድምህን አማኸው፥ ለእናትህም ልጅ ዕንቅፋት አኖርህ።
21ይህን አድርገህ ዝም አልሁህ፤ እኔ እንደ አንተ እሆን ዘንድ ጠረጠርህ፤ እዘልፍሃለሁ በፊትህም እቆማለሁ።
22እግዚአብሔርን የምትረሱ እናንተ፥ ይህን አስተውሉ፤ አለዚያ ግን ይነጥቃል የሚያድንም የለም።
23ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ።