English

ምዕራፍ 51

1አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ።
2ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤
3እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና።
4አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።
5እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።
6እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ።
7በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።
8ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል።
9ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።
10አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
11ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።
12የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ።
13ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፥ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።
14የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከደም አድነኝ፥ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች።
15አቤቱ፥ ከንፈሮቼን ክፈት፥ አፌም ምስጋናህን ያወራል።
16መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም።
17የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።
18አቤቱ፥ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጽሮች ሥራ።
19የጽድቁን መሥዋዕት መባውንም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በወደድህ ጊዜ፥ ያን ጊዜ በመሠዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሠዋሉ።