ምዕራፍ 59
1አምላኬ ሆይ፥ ከጠላቶቼ አድነኝ፤ በላዬም ከቆሙት አስጥለኝ።
2ከግፍ አድራጊዎች ታደገኝ፥ ከደም ሰዎችም አድነኝ።
3እነሆ፥ ነፍሴን ሸምቀውባታልና፥ ብርቱዎችም በላዬ ተሰበሰቡ። አቤቱ፥ በበደሌም አይደለም፥ በኃጢአቴም አይደለም።
4ያለ በደል ሮጥሁ ተዘጋጀሁም፤ ተነሥ፥ ተቀበለኝ፥ እይም።
5አንተም አቤቱ፥ የኃያላን አምላክ፥ የእስራኤል አምላክ፥ አሕዛብን ሁሉ ትጐበኛቸው ዘንድ ተነሥ፤ ዓመፅ የሚያደርጉትን ሁሉ አትማራቸው።
6ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ።
7እነሆ፥ በአፋቸው አሰምተው ይናገራሉ፤ ሰይፍም በከንፈሮቻቸው አለ፤ ማን ይሰማል? ይላሉ።
8አንተ ግን አቤቱ፥ ትሥቅባቸዋለህ፥ አሕዛብንም ሁሉ ትንቃቸዋለህ።
9እግዚአብሔር መጠጊያዬ ነውና ኃይሌን ወደ አንተ አስጠጋለሁ።
10የአምላኬ ቸርነቱ ይገናኘኛል አምላኬ በጠላቶቼ ላይ ያሳየኛል።
11ሕግህን እንዳይረሱ አትግደላቸው፤ አቤቱ ጋሻዬ፥ በኃይልህ በትናቸው አውርዳቸውም።
12ስለ አፋቸው ኃጢአት ስለ ከንፈራቸውም ቃል፥ መርገምንና ሐሰትን ስለሚናገሩ፥ በትዕቢታቸው ይጠመዱ።
13በቍጣ አጥፋቸው፥ እንዳይኖሩም አጥፋቸው፤ የያዕቆብም አምላክ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲገዛ ይወቁ።
14ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ።
15እነርሱም መብል ለመፈለግ ይበተኑ፤ ያልጠገቡ እንደ ሆነም ያንጐረጕራሉ።
16እኔ ግን ለኃይልህ እቀኛለሁ፤ በምሕረትህም ማልዶ ደስ ይለኛል፤ በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኸኛልና።
17ረዳቴ ሆይ፥ ለአንተ ለአምላኬ እዘምራለሁ፤ አንተ፥ አምላኬ፥ መጠጊያዬ ምሕረቴም ነህና።