ምዕራፍ 60
1አቤቱ፥ ጣልኸን አፈረስኸንም፤ ተቈጣኸን ይቅርም አልኸን።
2ምድርን አናወጥሃት አወክሃትም፤ ተናውጣለችና ቍስልዋን ፈውስ።
3ለሕዝብህ ጭንቅን አሳየሃቸው፥ አስደንጋጩንም ወይን አጠጣኸን።
4ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው።
5ወዳጆችህ እንዲድኑ በቀኝህ አድን፥ አድምጠኝም።
6እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ፤ ደስ ይለኛል፥ ሴኬምንም እካፈላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለሁ።
7ገለዓድ የእኔ ነው፥ ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው፤
8ሞዓብ መታጠቢያዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል።
9ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል?
10አቤቱ፥ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም።
11በመከራችን ረድኤትን ስጠን የሰውም ማዳን ከንቱ ነው።
12በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን እርሱ የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋልና።