ምዕራፍ 68
1እግዚአብሔር ይነሣ፥ ጠላቶቹም ይበተኑ፥ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ።
2ጢስ እንደሚበንን እንዲሁ ይብነኑ፤ ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ ኅጥኣን ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ።
3ጻድቃንም ደስ ይበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሐሤት ያድርጉ፥ በደስታም ደስ ይበላቸው።
4ለእግዚአብሔር ተቀኙ ለስሙም ዘምሩ፤ ወደ ምድረ በዳ ለወጣም መንገድ አድርጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው፥ በፊቱም ደስ ይበላችሁ፤ በፊቱም ይደነግጣሉ።
5እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው።
6እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።
7አቤቱ፥ በሕዝብም ፊት በወጣህ ጊዜ፥ በምድረ በዳም ባለፍህ ጊዜ፥ ምድር ተናወጠች፥
8ከሲና አምላክ ፊት፥ ከእስራኤል አምላክ ፊት ሰማያትም አንጠበጠቡ።
9አቤቱ፥ የሞገስን ዝናብ ለርስትህ አዘነብህ፥ በደከመም ጊዜ አንተ አጸናኸው።
10እንስሶችህ በውስጡ አደሩ፤ አቤቱ፥ በቸርነትህ ለድሆች አዘጋጀህ።
11እግዚአብሔር ቃሉን ሰጠ፤ የሚያወሩት ብዙ ሠራዊት ናቸው።
12የሠራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፤ በቤትም የምትኖር ምርኮን ተካፈለች።
13በርስቶች መካከል ብታድሩ፥ ከብር እንደ ተሠሩ እንደ ርግብ ክንፎች፥ በቅጠልያ ወርቅም እንደ ተለበጡ ላባዎችዋ ትሆናላችሁ።
14ሰማያዊ ንጉሥ በላይዋ ባዘዘ ጊዜ፥ በሰልሞን ላይ በረዶ ዘነበ።
15የእግዚአብሔር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፤ የጸና ተራራና የለመለመ ተራራ ነው።
16የጸኑ ተራራዎች ለምን ይነሣሉ? እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው፤ በእውነት እግዚአብሔር ለዘላለም ያድርበታል።
17የእግዚአብሔር ሰረገላዎች የብዙ ብዙ ሺህ ናቸው፤ ጌታ በመቅደሱ በሲና በመካከላቸው ነው።
18ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ።
19እግዚአብሔር አምላክ ቡሩክ ነው፤ እግዚአብሔር በየዕለቱ ቡሩክ ነው፤ የመድኃኒታችን አምላክ ይረዳናል።
20አምላካችንስ የደኅንነት አምላክ ነው፤ ከሞት መውጣትም ከእግዚአብሔር ነው።
21ነገር ግን እግዚአብሔር የጠላቶቹን ራስ፥ በኃጢአት የሚሄድንም የጠጕሩን አናት ይቀጠቅጣል።
22እግዚአብሔር እንዲህ አለ። ከባሳን አመጣቸዋለሁ፥ ከባሕርም ጥልቅ እመልሳቸዋለሁ፥
23እግሮችህ በደም ይረገጡ ዘንድ፥ የውሾችህ ምላስ በጠላቶች ላይ ይሆን ዘንድ።
24የአምላኬ የንጉሥ መንገድ በመቅደሱ፥ አቤቱ፥ መንገድህ ተገለጠ።
25አለቆች ቀደሙ፥ መዘምራንም ተከተሉ፤ ከበሮን በሚመቱ በቈነጃጅት መካከል።
26እግዚአብሔርን በጉባኤ፥ ጌታችንንም በእስራኤል ምንጭ አመስግኑት።
27ወጣቱ ብንያም በጕልበቱ በዚያ አለ፥ ገዦቻቸው የይሁዳ አለቆች የዛብሎን አለቆችና የንፍታሌምም አለቆች።
28አቤቱ፥ ኃይልህን እዘዝ፤ አቤቱ፥ ይህንም ለእኛ የሠራኸውን አጽናው።
29በኢየሩሳሌም ስላለው መቅደስህ ነገሥታት እጅ መንሻን ለአንተ ያመጣሉ።
30በሸምበቆ ውስጥ ያሉትን አራዊት፥ በአሕዛብ ውስጥ ያሉትን የበሬዎችንና የወይፈኖችን ጉባኤ ገሥጽ፥ እንደ ብር የተፈተኑት አሕዛብ እንዳይዘጉ፤ ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው።
31መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።
32የምድር ነገሥታት፥ ለእግዚአብሔር ተቀኙ፥ ለጌታም ዘምሩ።
33በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል።
34ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፤ ግርማው በእስራኤል ላይ፥ ኃይሉም በደመናት ላይ ነው።
35እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፤ የእስራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል፤ እግዚአብሔርም ይመስገን።