ምዕራፍ 69
1አቤቱ፥ ውኃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ።
2በጥልቅ ረግረግ ጠለቅሁ መቋሚያም የለኝም። ወደ ጥልቅ ባሕር ገባሁ ማዕበልም አሰጠመኝ።
3በጩኸት ደከምሁ ጕሮሮዬም ሰለለ፤ አምላኬን ስጠብቅ ዓይኖቼ ፈዘዙ።
4በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጕር በዙ፤ በዓመፅ ያሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ፤ በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ።
5አቤቱ፥ አንተ ስንፍናዬን ታውቃለህ፥ ኃጢአቴም ከአንተ አልተሰወረም።
6አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ ተስፋ የሚያደርጉህ በእኔ አይፈሩ፤ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ የሚሹህ በእኔ አይነወሩ።
7ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፥ እፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና።
8ለወንድሞቼ እንደ ሌላ፥ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው፥
9የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና።
10ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ።
11ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው።
12በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ፤ ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ።
13አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፤ አቤቱ፥ በምሕረትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ።
14እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ፤ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውኃ አስጥለኝ።
15የውኃው ማዕበል አያስጥመኝ፥ ጥልቁም አይዋጠኝ፥ ጕድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ።
16አቤቱ፥ ምሕረትህ መልካም ናትና ስማኝ። እንደ ርኅራኄህም ብዛት ወደ እኔ ተመልከት፤
17ከባሪያህም ፊትህን አትሰውር፤ ተጨንቄአለሁና ፈጥነህ አድምጠኝ።
18ነፍሴን ተመልክተህ ተቤዣት፤ ስለ ጠላቶቼም አድነኝ።
19አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፤ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው።
20ነፍሴ ስድብንና ኃሣርን ታገሠች፤ አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም። የሚያጽናናኝም አጣሁ።
21ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፥ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ።
22ማዕዳቸው በፊታቸው ለወጥመድ ለፍዳ ለዕንቅፋት ትሁንባቸው፤
23ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ጀርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ።
24መዓትህን በላያቸው አፍስስ፥ የቍጣህ መቅሠፍትም ያግኛቸው።
25ማደሪያቸው በረሃ ትሁን፥ በድንኳኖቻቸውም የሚቀመጥ አይገኝ፤
26አንተ የቀሠፍኸውን እነርሱ አሳድደዋልና፥ በቍስሌም ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩብኝ።
27በኃጢአታቸው ላይ ኃጢአትን ጨምርባቸው፥ በጽድቅህም አይግቡ።
28ከሕያዋን መጽሐፍ ይደምሰሱ፥ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ።
29እኔ ችግረኛና ቍስለኛ ነኝ፤ አቤቱ፥ የፊትህ መድኃኒት ይቀበለኝ።
30የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ፥ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።
31ቀንድና ጥፍር ካበቀለ ከእምቦሳ ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።
32ችግረኞች ያያሉ ደስ ይላቸዋል፤ እግዚአብሔርን ፈልጉ ሕያዋንም ሁኑ።
33እግዚአብሔር ችግረኞችን ሰምቶአልና፥ እስረኞቹንም አልናቀምና።
34ሰማይና ምድር ባሕርም በእርስዋም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመሰግኑታል።
35እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፥ የይሁዳንም ከተሞች ይሠራልና፤ በዚያም ይቀመጣሉ ይወርሱአትማል።
36የባሪያዎቹ ዘር ይኖሩባታል። ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይቀመጣሉ።