ምዕራፍ 1
1የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤
2ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፥
3የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል፥
4ብልሃትን ለአላዋቂዎች ይሰጥ ዘንድ ለጐበዛዝትም እውቀትንና ጥንቃቄን፥
5ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፥ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል።
6ምሳሌንና ትርጓሜን የጠቢባንና ቃልና የተሸሸገውን ነገር ለማስተዋል።
7የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
8ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናንትህንም ሕግ አትተው፤
9ለራስህ የሞገስ ዘውድ ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና።
10ልጄ ሆይ፥ ኃጢአተኞች ቢያባብሉህ እሺ አትበል።
11ደምን ለማፍሰስ ለእኛ ጋር ና እናድባ፥ ለንጹሕም ያለ ምክንያት ወጥመድን እንሸምቅበት ቢሉ፤
12በሕይወታቸው ሳሉ እንደ ሲኦል ሆነን እንዋጣቸው፥ በሙሉም ወደ ጕድጓድ እንደሚወድቁ ይሁኑ፤
13መልካሙን ሀብት ሁሉ እናገኛለን፥ ከምርኮውም ቤታችንን እንሞላለን፤
14ዕጣህን ከእኛ ጋር ጣል፤ ለሁላችንም አንድ ከረጢት ይሁን ቢሉ፤
15ልጄ ሆይ፥ ከእነርሱ ጋር በመንገድ አትሂድ፥ ከጎዳናቸውም እግርህን ፈቀቅ አድርግ፤
16እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉና፥ ደም ለማፍሰስም ይፈጥናሉና።
17መርበብ በወፎች ዓይን ፊት በከንቱ ትተከላለችና።
18እነርሱም በደማቸው ላይ ያደባሉ፥ በነፍሳቸውም ላይ ይሸምቃሉ።
19እንዲሁ ይህ መንገድ ትርፍን ለማግኘት የሚሳሳ ሁሉ ነው። የባለቤቱን ነፍስ ይነጥቃል።
20ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች፤ በአደባባይ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፤
21በአደባባይ ትጣራለች፤ በከተማይቱ መግቢያ በር ቃልን ትናገራለች።
22እናንተ አላዋቂዎች፥ እስከ መቼ አላዋቂነት ትወድዳላችሁ? ፌዘኞችም ፌዝን ይፈቅዳሉ? ሰነፎችም እውቀትን ይጠላሉ?
23ወደ ዘለፋዬ ተመለሱ፤ እነሆ፥ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ፤ ቃሌን አስተምራችኋለሁ።
24በጠራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁ፥ እጄን በዘረጋሁ ጊዜ ማንም ስላላስተዋለ፥
25ምክሬን ሁሉ ግን ቸል ስላላችሁ፥ ዘለፋዬንም ስላልፈቀዳችሁ፤
26እኔም ስለዚህ በጥፋታችሁ እስቃለሁ፤ ጥፋታችሁም በመጣ ጊዜ አላግጥባችvሁ።
27ድንጋጤ እንደ ጐርፍ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ ጥፋታችሁም እንደ ዐውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ፥ ጭንቅና መከራ በወረደባችሁ ጊዜ።
28የዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፥ እኔ ግን አልመልስም፤ ተግተው ይሹኛል፥ ነገር ግን አያገኙኝም።
29እውቀትን ጠልተዋልና፥ እግዚአብሔርንም መፍራት አልመረጡምና፤
30ምክሬን አልፈቀዱምና፥ ዘለፋዬንም ሁሉ ንቀዋልና፤
31ስለዚህ የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፥ ከራሳቸው ምክር ይጠግባሉ።
32አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሰነፎችንም ቸልተኛ መሆን ያጠፋቸዋልና።
33የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል።