ምዕራፍ 2
1ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥
2ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ።
3ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥
4እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤
5የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።
6እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤
7እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፤
8የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል።
9የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ።
10ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤
11ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥
12ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፥ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፤
13እነርሱም በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና የሚተው፥
14ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ደስታን የሚያደርጉ፥
15መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ናቸው፤
16ከጋለሞታ ሴት አንተን ለመታደግ፥ ቃልዋን ከምታለዝብ ከሌላዪቱም ሴት፤
17የሕፃንነት ወዳጅዋን የምትተው የአምላክዋንም ቃል ኪዳን የምትረሳ፤
18ቤትዋ ወደ ሞት ያዘነበለ ነው፥ አካሄድዋም ወደ ሙታን ጥላ።
19ወደ እርስዋ የሚገቡ ሁሉ አይመለሱም፥ የሕይወትንም ጎዳና አያገኙም፤
20አንተም በደጋግ ሰዎች መንገድ እንድትሄድ የጻድቃንንም ጎዳና እንድትጠብቅ።
21ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፥ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤
22ኃጥኣን ግን ከምድር ይጠፋሉ፥ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።