ምዕራፍ 10
1የሰሎሞን ምሳሌዎች። ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው።
2በኃጢአት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል።
3እግዚአብሔር የጻድቁን ነፍስ አያስርብም፤ የኅጥኣንን ምኞት ግን ይገለብጣል።
4የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች።
5በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል።
6በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፤ የኅጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል።
7የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤ የኅጥኣን ስም ግን ይጠፋል።
8በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፤ በከንፈሩ የሚሰንፍ ግን ይወድቃል።
9ያለ ነውር የሚሄድ ተማምኖ ይሄዳል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል።
10በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል፤ ደፍሮ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል።
11የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ናት፤ የኃጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል።
12ጥል ክርክርን ታስነሣለች፤ ፍቅር ግን ኃጢአትን ሁሉ ትከድናለች።
13በብልሃተኛ ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፤ በትር ግን አእምሮ ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው።
14ጠቢባን እውቀትን ይሸሽጋሉ፤ የሰነፍ አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል።
15የባለጠጋ ሀብት ለእርሱ የጸናች ከተማ ናት፤ የድሆች ጥፋት ድህነታቸው ነው።
16የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፤ የኃጥእ ፍሬ ግን ለኃጢአት ነው።
17ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳል፤ ዘለፋን የሚተው ግን ይስታል።
18ጥልን የሚከድን ሐሰተኛ ከንፈር አለው፤ ሐሜትንም የሚገልጥ ሰነፍ ነው።
19በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው።
20የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፤ የኅጥኣን ልብ ግን ምናምን ነው።
21የጻድቅ ከንፈሮች ብዙ ሰዎችን ይመግባሉ፤ ሰነፎች ግን ከልባቸው ጕድለት የተነሣ ይሞታሉ።
22የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።
23ክፉ ነገር ማድረግ ለሰነፍ ሰው ጨዋታ ነው፤ እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው።
24የኀጥእ ሰው ፍርሃት በላዩ ይመጣበታል፥ ለጻድቃንም ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች።
25ዐውሎ ነፋስ ሲያልፍ ኃጥእ አይገኝም፤ ጻድቅ ግን የዘላለም መሠረት ነው።
26ሆምጣጤ ጥርስን፥ ጢስም ዓይንን እንደሚጐዳ፥ እንዲሁም ታካች ለላኩት።
27እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፤ የኀጥኣን ዕድሜ ግን ታጥራለች።
28የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤ የኀጥኣን ተስፋ ግን ይጠፋል።
29የእግዚአብሔር መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው፥ ጥፋት ግን ክፋትን ለሚያደርጉ።
30ጻድቃን ለዘላለም አይናወጡም፤ ኅጥኣን ግን በምድር ላይ አይቀመጡም።
31የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤ ጠማማ ምላስ ግን ትቈረጣለች።
32የጻድቅ ከንፈሮች ደስ የሚያሰኝ ነገርን ያውቃሉ፤ የኀጥኣን አፍ ግን ጠማማ ነው።