ምዕራፍ 9
1ጥበብ ቤትዋን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶችዋን አቆመች።
2ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋን ደባለቀች፥ ማዕድዋን አዘጋጀች።
3ባሪያዎችዋን ልካ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ጠራች።
4አላዋቂ የሆነ ወደዚህ ፈቀቅ ይበል፤ አእምሮ የጐደላቸውንም እንዲህ አለች።
5ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ የደባለቅሁትንም የወይን ጠጅ ጠጡ።
6አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ።
7ፌዘኛን የሚገሥጽ ለራሱ ስድብን ይቀበላል፥ ኅጥአንም የሚዘልፍ ነውርን ያገኛል።
8ፌዘኛን አትገሥጽ እንዳይጠላህ፤ ጠቢብን ገሥጽ ይወድድህማል።
9ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፥ ጥበብንም ያበዛል፤ ጽድቅንም አስተምረው፥ እውቀትንም ያበዛል።
10የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው።
11ዘመንህ በእኔ ይበዛልና፥ የሕይወትህም ዕድሜ ይጨመርልሃልና።
12ጠቢብ ብትሆን ለራስህ ጠቢብ ትሆናለህ፥ ፌዘኛም ብትሆን ፌዘኛነትህን ለብቻህ ትሸከማለህ። ፍን [የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።] ልጄ ለራስህ አዋቂ ብትሆን ለባልንጀራህም አዋቂ ትሆናለህ፤ ለራስህ ክፉ ብትሆን ግን ክፋትህን ትማራለህ። ሐሰትን የሚያዘጋጅ ሰው ነፋሳትን እንደሚያዘጋጅ ሰው ነው፤ የሚበርር ወፍንም እንደሚከተል ይመስላል። የወይኑ ቦታ መንገዱን ተወ፤ የሚሠማራባትን መንገድ ዘነጋ፤ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል ለጥም ወደ ተሠራች አገር ይሄዳል፤ የማያፈራ የማይጠቅም ገንዘብንም በእጁ ይሰበስባል።
13ሰነፍ ሴት ሁከተኛ ናት፤ አሳብ የላትም፥ አንዳችም አታውቅም።
14በቤትዋ ደጅ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ በወንበር ላይ ትቀመጣለች፥
15በመንገድ የሚያልፉትን አካሄዳቸውንም ያቀኑትን ለመጥራት።
16አላዋቂ የሆነ ወደዚህ ፈቀቅ ይበል፤ አእምሮ የጐደለውንም እንዲህ አለች።
17የስርቆት ውኃ ይጣፍጣል፥ የተሸሸገም እንጀራ ደስ ያሰኛል።
18ነገር ግን እርሱ ሙታን ከዚያ እንዳሉ፥ እድምተኞችዋም በሲኦል ጥልቀት እንዳሉ አያውቅም።