English

ምዕራፍ 15

1የለዘበች መልስ ቍጣን ትመልሳለች ሸካራ ቃል ግን ቍጣን ታስነሣለች።
2የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል፤ የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናን ያፈልቃል።
3የእግዚአብሔር ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ።
4ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፤ የጠማማ ምላስ ግን ነፍስን ይሰብራል።
5ሰነፍ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፤ ዘለፋን የሚቀበል ግን አእምሮው የበዛ ነው።
6በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፤ የኃጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው።
7የጠቢባን ከንፈር እውቀትን ትዘራለች፤ የሰነፎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም።
8የኅጥኣን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው።
9የኅጥኣን መንገድ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እርሱ ግን ጽድቅን የሚከተል ይወድዳል።
10ክፉ መቅሠፍት መንገድን በተወ ሰው ላይ ይመጣል፥ ዘለፋንም የሚጠላ ይሞታል።
11ሲኦልና ጥፋት በእግዚአብሔር ፊት የታወቁ ናቸው፤ ይልቁንም የሰዎች ልብ የታወቀ ነው።
12ፌዘኛ ሰው የሚዘልፈውን አይወድድም፥ ወደ ጠቢባንም አይሄድም።
13ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፤ በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች።
14የአዋቂ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፤ የሰነፎች አፍ ግን በስንፍና ይሰማራል።
15ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፤ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው።
16እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል።
17የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።
18ቍጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ ትዕግሥተኛ ሰው ግን ጸጥ ያሰኘዋል።
19የታካች መንገድ እንደ እሾህ አጥር ናት፤ የጻድቃን መንገድ ግን የተደላደለች ናት።
20ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል።
21ልብ ለሌለው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፤ አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀናል።
22ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል።
23ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፤ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው!
24በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል።
25እግዚአብሔር የትዕቢተኞች ቤት ይነቅላል፤ የባልቴትን ዳርቻ ግን ያጸናል።
26የበደለኛ አሳብ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናት፤ ያማረ ቃል ግን ጥሩ ነው።
27ትርፍ ለማግኘት የሚሳሳ ሰው የራሱን ቤት ያውካል፤ መማለጃን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል።
28የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል የኅጥኣን አፍ ግን ክፋትን ያፈልቃል።
29እግዚአብሔር ከኅጥኣን ይርቃል፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።
30የዓይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል፥ መልካም ወሬም አጥንትን ያለመልማል።
31የሕይወትን ተግሣጽ የሚሰማ ጆሮ በጠቢባን መካከል ይኖራል።
32ተግሣጽን ቸል የሚል የራሱን ነፍስ ይንቃል፤ ዘለፋን የሚሰማ ግን አእምሮ ያገኛል።
33እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ትምህርት ነው፤ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።