ምዕራፍ 16
1የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው፤ የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
2የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኖቹ ፊት ንጹሕ ነው፤ እግዚአብሔር ግን መንፈስን ይመዝናል።
3ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ አሳብህም ትጸናለች።
4እግዚአብሔር ሁሉን ለእርሱ ለራሱ ፈጠረ፥ ኀጥእን ደግሞ ለክፉ ቀን።
5በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው፥ እጅ በእጅም ሳይቀጣ አይቀርም።
6በምሕረትና በእውነት ኃጢአት ትሰረያለች፥ እግዚአብሔርንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል።
7የሰው አካሄድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘው እንደ ሆነ፤ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል።
8በጽድቅ የሚገኝ ጥቂት ነገር በዓመፅ ከሚገኝ ከብዙ ትርፍ ይሻላል።
9የሰው ልብ መንገዱ ያዘጋጃል፤ እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቀናለታል።
10የእግዚአብሔር ብይን በንጉሥ አፍ ነው፥ አፉም በፍርድ አይስትም።
11እውነተኛ ሚዛንና መመዘኛ የእግዚአብሔር ናቸው፤ የከረጢት መመዘኛዎች ሁሉ የእርሱ ሥራ ናቸው።
12ግፍን መሥራት በንጉሥ ዘንድ ጸያፍ ነገር ነው፥ ዙፋን በጽድቅ ይጸናልና።
13የጽድቅ ከንፈር የነገሥታት ደስታ ናት፥ በቅን የሚናገር እርሱንም ይወድዱታል።
14የንጉሥ ቍጣ እንደ ሞት መልእክተኛ ነው፤ ጠቢብ ሰው ግን ያቈላምጠዋል።
15በንጉሥ ፊት ብርሃን ዘንድ ሕይወት አለ፥ መልካም ፈቃዱም እንደ በልግ ዝናብ ደመና ነው።
16ጥበብን ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል! ማስተዋልንም ማግኘት ከብር ይልቅ የሚመረጥ ነው።
17የቅኖች መንገድ ከክፋት መራቅ ነው፤ መንገዱን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃታል።
18ትዕቢት ጥፋትን፥ ኵሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።
19ከዕቡያን ጋር ምርኮ ከመካፈል ከትሑታን ጋር በተዋረደ መንፈስ መሆን ይሻላል።
20ቃልን የሚያዳምጥ መልካም ነገርን ያገኛል፤ በእግዚአብሔር የታመነ ምስጉን ነው።
21ልቡ ጠቢብ የሆነ አስተዋይ ይባላል፥ በከንፈሩም ጣፋጭ የሆነ ትምህርትን ያበዛል።
22ገንዘብ ላደረገው ሰው እውቀት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ስንፍና ግን የሰነፎች ቅጣት ነው።
23የጠቢብ ልብ አፉን ያስተምራል፥ ለከንፈሩም ትምህርትን ይጨምራል።
24ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፤ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው።
25ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።
26የሠራተኛ ራብ ለእርሱ ይሠራል፥ አፉ ይጐተጕተዋልና።
27ምናምንቴ ሰው ክፋትን ይምሳል፥ በከንፈሩም የሚቃጠል እሳት አለ።
28ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፤ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል።
29ግፈኛ ሰው ወዳጁን ያባብላል፥ መልካምም ወዳይደለ መንገድ ይመራዋል።
30ዓይኑን የሚዘጋ ጠማማ አሳብን ያስባል፤ ከንፈሩን የሚነክስ ክፋትን ይፈጽማል።
31የሸበተ ጠጕር የክብር ዘውድ ነው፥ እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል።
32ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፥ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስዱ ይበልጣል።
33ዕጣ በጕያ ይጣላል፤ መደብዋ ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።