English

ምዕራፍ 19

1በከንፈሩ ከሚወሳልት ሰነፍ ይልቅ ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል።
2ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ እግሩንም የሚያፈጥን ከመንገድ ይስታል።
3የሰው ስንፍና መንገዱን ታጣምምበታለች፤ ልቡም በእግዚአብሔር ላይ ይቈጣል።
4ባለጠግነት ብዙ ወዳጆች ይጨምራል፤ የድሀ ወዳጅ ግን ከእርሱ ይርቃል።
5ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፥ በሐሰትም የሚናገር አያመልጥም።
6ብዙ ሰዎች ለጋሱን ያቈላምጣሉ፥ ስጦታ ለሚሰጥም ሁሉ ወዳጅ ነው።
7ድሀን ሰው ወንድሞቹ ሁሉ ይጠሉታል፤ ይልቁንም ወዳጆቹ ከእርሱ ይርቃሉ። እነርሱንም በቃል ቢከተላቸው አንዳች አይረቡትም።
8ጥበብን የሚያገኝ ነፍሱን ይወድዳል፥ ማስተዋልንም የሚጠብቅ መልካም ነገርን ያገኛል።
9ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፤ በሐሰትም የሚናገር ይጠፋል።
10ለሰነፍ ቅምጥልነት አይገባውም፥ ይልቁንም ባሪያ በአለቆች ላይ ይገዛ ዘንድ።
11ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቍጣ ያዘገየዋል፥ ለበደለኛውም ይቅር ይል ዘንድ ክብር ይሆንለታል።
12እንደ አንበሳ ግሣት የንጉሥ ቍጣ ነው፥ ሞገሱም በመስክ ላይ እንዳለ ጠል ነው።
13ሰነፍ ልጅ ለአባቱ ኀዘን ነው፥ ጠበኛም ሚስት እንደማያቋርጥ ነጠብጣብ ናት።
14ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት።
15ተግባር መፍታት እንቅልፍን ታመጣለች፥ የታካችም ነፍስ ትራባለች።
16ትእዛዝን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ መንገዱን ቸል የሚል ግን ይጠፋል።
17ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል።
18ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥጽ፥ መሞቱንም አትሻ።
19ንዴተኛ ሰው መቀጮ ይከፍላል፤ ብታድነውም ደግሞ ትጨምራለህ።
20ምክርን ስማ፥ ተግሣጽንም ተቀበል በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ።
21በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል።
22የሰው ቸርነት የእርሱ ፍሬ ነው፤ ከሐሰተኛ ባለጠጋም እውነተኛ ድሀ ይሻላል።
23እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤ የሚፈራውም ጠግቦ ይኖራል፥ ክፉ ነገርም አያገኘውም።
24ታካች ሰው እጁን በወጭቱ ያጠልቃታል፥ ወደ አፉ ስንኳ አይመልሳትም።
25ፌዘኛ ብትገርፈው አላዋቂ ብልሃተኛ ይሆናል፤ አስተዋይን ሰው ብትገሥጸው እውቀትን ያገኛል።
26አባቱን የሚያስከፋ እናቱንም የሚያሳድድ የሚያሳፍርና ጐስቋላ ልጅ ነው።
27ልጅ ሆይ፥ ተግሣጽን ከሰማህ በኋላ ከእውቀት ቃል መሳሳትን ተው።
28ወስላታ ምስክር በፍርድ ያፌዛል፥ የኀጥኣንም አፍ ክፋትን ይውጣል።
29ለሚያፌዙ ሰዎች ፍርድ ተዘጋጅታለች፥ ለሰነፎችም ጀርባ በትር።