ምዕራፍ 20
1የወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል፥ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በዚህም የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም።
2የንጉሥ ቍጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፤ የሚያስቈጣውም ሰው የራሱን ነፍስ ይበድላል።
3ከክርክር ይርቅ ዘንድ ለሰው ክብሩ ነው፤ ሰነፍ ሁሉ ግን እንዲህ ባለ ነገር ይጣመራል።
4ታካች ሰው በብርድ ምክንያት አያርስም፤ ስለዚህ በመከር ይለምናል፥ ምንም አያገኝም።
5ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል።
6ብዙ ሰዎች ቸርነታቸውን ያወራሉ፤ የታመነውን ሰው ግን ማን ያገኘዋል?
7ጻድቅ ያለ ነውር ይሄዳል፥ ልጆቹም ከእርሱ በኋላ ምስጉኖች ናቸው።
8በፍርድ ወንበር የተቀመጠ ንጉሥ ክፉውን ሁሉ በዓይኖቹ ይበትናል።
9ልቤን አነጻሁ፥ ከኃጢአትም ጠራሁ የሚል ማን ነው?
10ሁለት ዓይነት ሚዛንና ሁለት ዓይነት መስፈሪያ፥ ሁለቱ በእግዚአብሔር ፊት ርኩሳን ናቸው።
11ሕፃን ቅንና ንጹሕ መሆኑ በሚያደርገው ሥራ ይታወቃል።
12የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፥ ሁለቱን እግዚአብሔር ፈጠራቸው።
13ድሀ እንዳትሆን እንቅልፍን አትውደድ፤ ዓይንህን ክፈት፥ እንጀራም ትጠግባለህ።
14የሚገዛ ሰው። ክፉ ነው ክፉ ነው ይላል፤ በሄደ ጊዜ ግን ይመካል።
15ወርቅና ብዙ ቀይ ዕንቍ ይገኛል፤ የእውቀት ከንፈር ግን የከበረች ጌጥ ናት።
16ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው።
17የሐሰት እንጀራ ለሰው የጣፈጠ ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን አፉ ጭንጫ ይሞላል።
18አሳብ በምክር ትጸናለች፥ በመልካምም ምክር ሰልፍ አድርግ።
19ዘዋሪ ሐሜተኛ ምሥጢርን ይገልጣል፤ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ሰውን አትገናኘው።
20አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ፥ በጽቅድቅ ጨለማ መብራቱ ይጠፋል።
21በመጀመሪያ ፈጥኖ የተከማቸ ርስት ፍጻሜው አይባረክም።
22ክፉ እመልሳለሁ አትበል፤ እግዚአብሔርን ተማመን፥ እርሱም ያድንሃል።
23ሁለት ዓይነት ሚዛን በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ ሐሰተኛ ሚዛንም መልካም አይደለም።
24የሰው አካሄዱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ እንግዲያስ ሰው መንገዱን እንዴት ያስተውላል?
25ሰው በችኰላ። ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው ብሎ ቢሳል፥ ከተሳለም በኋላ ቢፀፀት ወጥመድ ነው።
26ጠቢብ ንጉሥ ኀጥኣንን በመንሽ ይበትናቸዋል፥ መንኰራኵሩንም በእነርሱ ላይ ያንኰራኵርባቸዋል።
27የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው የሆዱን ጕርጆች ሁሉ የሚመረምር።
28ቸርነትና እውነት ንጉሥን ይጠብቁታል፤ ዙፋኑም በቸርነት ይበረታል።
29የጎበዛዝት ክብር ጕልበታቸው ናት፥ የሽማግሌዎችም ጌጥ ሽበት ነው።
30የሰንበር ቍስል ክፉዎችን ያነጻል፤ ግርፋትም ወደ ሆድ ጕርጆች ይገባል።