ምዕራፍ 23
1ከመኰንን ጋር ለመብላት በተቀመጥህ ጊዜ፥ በፊትህ ያለውን በደኅና አስተውል፤
2ሰውነትህም ቢሳሳ፥ በጕሮሮህ ላይ ካራ አድርግ።
3ጣፋጩ መብል አይመርህ የሐሰት እንጀራ ነውና።
4ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው።
5በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና።
6የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤
7በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም።
8የበላኸውን መብል ትተፋዋለህ፥ ያማረውንም ቃልህን ታጠፋዋለህ።
9በሰነፍ ጆሮ አንዳች አትናገር፥ የቃልህን ጥበብ ያፌዝብሃልና።
10የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ፤ ወደ ድሀ አደጎች እርሻ አትግባ፤
11ታዳጊአቸው ጽኑ ነውና፥ እርሱም ፍርዳቸውን ከአንተ ጋር ይፋረዳልና።
12ልብህን ለተግሣጽ ስጥ፥ ጆሮህንም ወደ እውቀት ቃል።
13ሕፃንን ከመቅጣት ቸል አትበል፥ በበትር ብትመታው አይሞትምና።
14በበትር ትመታዋለህ፥ ነፍሱንም ትታደጋለህ።
15ልጄ ሆይ፥ ልብህ ጠቢብ ቢሆን ልቤ ደግሞ ደስ ይለዋል፤
16ከንፈሮችህም በቅን ቢናገሩ ኵላሊቶቼ ደስ ይላቸዋል።
17ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር፤
18በእውነት ፍጻሜ አለህና፥ ተስፋህም አይጠፋምና።
19ልጄ ሆይ፥ ስማ ጠቢብም ሁን ልብህንም በቀናው መንገድ ምራ።
20የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ ለሥጋም ከሚሣሡ ጋር፤
21ሰካርና ሆዳም ይደኸያሉና፥ የእንቅልፍም ብዛት የተቦጫጨቀ ጨርቅ ያስለብሳልና።
22የወለደህን አባትህን ስማ፥ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።
23እውነትን ግዛ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም።
24የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፥ ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሤትን ያገኛል።
25አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፥ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት።
26ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ፤
27ጋለሞታ ሴት የጠለቀች ዐዘቅት ናትና፥ ሌላይቱም ሴት የጠበበች ጕድጓድ ናትና።
28እንደ ሌባ ታደባለች ወስላቶችንም በሰው ልጆች መካከል ታበዛለች።
29ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው?
30የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን?
31ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፥ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፥ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ።
32በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል።
33ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል።
34በባሕር ውስጥ እንደ ተኛ ትሆናለህ፥ በደቀልም ላይ እንደ ተኛ።
35መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም፤ ጐሰሙኝ፥ አላወቅሁምም። መቼ እነሣለሁ? ደግሞ ጨምሬ እሻታለሁ ትላለህ።