English

ምዕራፍ 29

1ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፥ ፈውስም የለውም።
2ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል፤ ኀጥኣን በሠለጠኑ ጊዜ ግን ሕዝብ ያለቅሳል።
3ጥበብን የወደደ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ጋለሞቶችን የሚከተል ግን ሀብቱን ያጠፋል።
4ንጉሥ በፍርድ አገሩን ያጸናል፤ መማለጃ የሚወድድ ግን ያፈርሰዋል።
5ወዳጁን በለዘበ ቃል የሚናገር ሰው ለእግሩ መርበብን ይዘረጋል።
6በክፉ ሰው ዓመፃ ወጥመድ ይገኛል፤ ጻድቅ ግን ደስ ይለዋል፥ እልልም ይላል።
7ጻድቅ የድሆችን ፍርድ ይመለከታል፤ ኀጥእ ግን እውቀትን አያስተውልም።
8ፌዘኞች ከተማቸውን ያቃጥላሉ፤ ጠቢባን ግን ቍጣን ይመልሳሉ።
9ጠቢብ ከሰነፍ ጋር ቢጣላ፥ ሰነፍ ወይም ይቈጣል ወይም ይስቃል፥ ዕረፍትም የለም።
10ደምን ለማፍሰስ የሚሹ ሰዎች ፍጹሙን ሰው ይጠላሉ፥ ደግሞም የቅኑን ሰው ነፍስ ይሻሉ።
11ሰነፍ ሰው ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል።
12መኰንን ሐሰተኛ ነገርን ቢያደምጥ፥ ከእርሱ በታች ያሉት ሁሉ ዓመፅኞች ይሆናሉ።
13ድሀና ግፈኛ ተገናኙ፤ እግዚአብሔር የሁለቱንም ዓይን ያበራል።
14ለድሀ በእውነት የሚፈርድ ንጉሥ፥ ዙፋኑ ለዘላለም ይጸናል።
15በትርና ተግሣጽ ጥበብን ይሰጣሉ፤ ያልተቀጣ ብላቴና ግን እናቱን ያሳፍራል።
16ኀጥኣን ሲበዙ ኃጢአት ትበዛለች፤ ጻድቃን ግን ውደቀታቸውን ያያሉ።
17ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሰጥሃል፤ ለነፍስህም ተድላን ይሰጣታል።
18ራእይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተመሰገነ ነው።
19ባሪያ በቃል አይገሠጽም፤ ቢያስተውል እንኳ አይመልስምና።
20በቃሉ የሚቸኵለውን ሰው ብታይ፥ ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው።
21ባሪያውን ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማቀማጠል የሚያሳድግ የኋላ ኋላ እንደ ጌታ ያደርገዋል።
22ቍጡ ሰው ክርክርን ያነሣሣል። ወፈፍተኛ ሰውም ኃጢአትን ያበዛል።
23ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤ መንፈሱን የሚያዋርድ ግን ክብርን ይቀበላል።
24ከሌባ ጋር የሚካፈል ነፍሱን ይጠላል፤ መርገምን ይሰማል፥ ነገር ግን ምንም አይገልጥም።
25ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል።
26ብዙ ሰዎች የሹምን ፊት ይሻሉ፤ የሰው ፍርድ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
27ኃጢአተኛ በጻድቃን ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ በቀና መንገድ የሚሄደውም በኀጥኣን ዘንድ አስጸያፊ ነው።