English

ምዕራፍ 30

1የማሣ አገር ሰው የያቄ ልጅ የአጉር ቃል ሰውየው ለኢቲኤልና ለኡካል እንደዚህ ይናገራል።
2እኔ በእውነት ከሰው ሁሉ ይልቅ ደንቆሮ ነኝ፥ የሰውም ማስተዋል የለብኛም።
3ጥበብንም አልተማርሁም፥ ቅዱሱንም አላወቅሁትም።
4ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው? ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?
5የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች፤ እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው።
6እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር።
7ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ፤
8ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፤ ድኅነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥
9እንዳልጠግብ እንዳልክድህም። እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።
10እንዳይሰድብህ በደለኛም እንዳትሆን ባሪያን በጌታው ፊት አትማ።
11አባቱን የሚረግም፥ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ።
12ለራሱ ንጹሕ የሆነ የሚመስለው ከርኵሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ።
13ከፍ ከፍ ያሉ ዓይኖች ያሉት፥ ሽፋሽፍቶቹም ወደ ላይ የሚያዩ ትውልድ አለ።
14ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ አለ።
15አልቅት። ስጠን ስጠን የሚሉ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉት። ሦስቱ የማይጠግቡ አራቱም። በቃን የማይሉ ናቸው፤
16እነርሱም ሲኦልና የማትወልድ ማኅፀን ውኃ የማትጠግብ ምድርና። በቃኝ የማትል እሳት ናቸው።
17በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዓይን የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል።
18ሦስት ነገር ይገርመኛል፥ አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም።
19እነርሱም የንስር መንገድ በሰማይ፥ የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፥ የመርከብ መንገድ በባሕር ላይ፥ የሰውም መንገድ ከቈንጆ ጋር ናቸው።
20እንዲሁ በልታ አፍዋን የምታብስ። አንዳች ክፉ ነገር አላደረግሁም የምትልም የአመንዝራ ሴት መንገድ ናት።
21በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥ አራተኛውንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም።
22ባሪያ በነገሠ ጊዜ ሰነፍም እንጀራ በጠገበ ጊዜ፥
23የተጠላች ሴት ባል ባገኘች ጊዜ፥ ሴት ባሪያም እመቤቷን በወረሰች ጊዜ።
24በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፤ እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፤
25ገብረ ጕንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸዋን ይሰበስባሉ።
26ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው፥ ቤታቸውን ግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ።
27አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም፥ ሁላቸው ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ።
28እንሽላሊት በእጅ ይያዛል፥ በነገሥታት ግቢ ግን ይኖራል።
29መልካም አረማመድን የሚራመዱ ሦስት ፍጥረቶች አሉ፥ አራተኛውም መልካም አካሄድን ይሄዳል፤
30የአንበሳ ደቦል ከእንስሳ ሁሉ የሚበረታ፥ የማይመለስ፥ እንስሳንም የማይፈራ፤
31በእንስቶች መካከል በድፍረት የሚራመድ አውራ ዶሮ፤ መንጋን የምመራ አውራ ፍየል፤ በሕዝብ ፊት በግልጥ የሚናገር ንጉሥ።
32ከፍ ከፍ ስትል ስንፍናን ያደረግህ እንደሆነ፥ ክፉም ያሰብህ እንደ ሆነ፥ እጅህን በአፍህ ላይ ጫን።
33ወተት መግፋት ቅቤን ያወጣል፥ አፍንጫንም መጭመቅ ደምን ያወጣ፤ እንዲሁም ቍጣን መጐተት ጠብን ያወጣል።