English

ምዕራፍ 4

1እናንተ ልጆች፥ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፥ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ፤
2መልካም ትምህርትን እሰጣችኋለሁና፤ ሕጌን አትተዉ።
3እኔም አባቴን የምሰማ ልጅ ነበርሁና፥ በእናቴም ዘንድ እወደድ ነበር።
4ያስተምረኝም ነበር እንዲህም ይለኝ ነበር። ልብህ ቃሌን ይቀበል፤ ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ።
5ጥበብን አግኝ፤ ማስተዋልን አግኝ፤ አትርሳም፥ ከአፌም ቃል ፈቀቅ አትበል።
6አትተዋት፥ ትደግፍህማለች፤ ውደዳት፥ ትጠብቅህማለች።
7ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ፤ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ።
8ከፍ ከፍ አድርጋት፥ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ ብታቅፋትም ታከብርሃለች።
9ለራስህ የሞገስ አክሊልን ትሰጥሃለች፥ የተዋበ ዘውድንም ታበረክትሃለች።
10ልጄ ሆይ፥ ስማ፥ ንግግሬንም ተቀበል፤ የሕይወትህም ዘመን ትበዛልሃለች።
11የጥበብን መንገድ አስተማርሁህ፤ በቀናች ጎዳና መራሁህ።
12በሄድህ ጊዜ እርምጃህ አይጠብብም፤ በሮጥህም ጊዜ አትሰናከልም።
13ተግሣጽን ያዝ፥ አትተውም፤ ጠብቀው፥ እርሱ ሕይወትህ ነውና።
14በኃጥኣን መንገድ አትግባ፥ በክፉ ሰዎችም ጎዳና አትሂድ።
15ከእርስዋ ራቅ፥ አትሂድባትም፤ ፈቀቅ በል ተዋትም።
16ክፉ ካላደረጉ አይተኙምና፥ ካላሰናከሉም እንቅልፋቸው ይወገዳልና።
17የኃጢአትን እንጀራ ይበላሉና፥ የግፍንም ወይን ጠጅ ይጠጣሉና።
18የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።
19የኃጥኣን መንገድ እንደ ጨለማ ነው፥ እንዴት እንደሚሰናከሉም አያውቁም።
20ልጄ ሆይ፥ ንግግሬን አድምጥ ወደ ቃሌም ጆሮህን አዘንብል።
21ከዓይንህ አታርቃት፥ በልብህም ውስጥ ጠብቃት።
22ለሚያገኙአት ሕይወት፥ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ነውና።
23አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።
24የአፍህን ጠማማነት ከአንተ አውጣ፥ ሐሰተኞቹን ከንፈሮችም ከአንተ አርቅ።
25ዓይኖችህ አቅንተው ይዩ፥ ሽፋሽፍቶችህም በቀጥታ ይመልከቱ።
26የእግርህን መንገድ አቅና፥ አካሄድህም ሁሉ ይጽና።
27ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤ እግርህንም ከክፉ መልስ።