ምዕራፍ 5
1ልጄ ሆይ፥ ወደ ጥበቤ አድምጥ፤ ጆሮህን ወደ ትምህርቴ መልስ፥
2ጥንቃቄን ትጠብቅ ዘንድ ከንፈሮችህም እውቀትን እንዲጠብቁ።
3ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥ አፍዋም ከቅቤ የለሰለሰ ነውና፤
4ፍጻሜዋ ግን እንደ እሬት የመረረ ነው፥ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍም የተሳለ ነው።
5እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ፥ አረማመድዋም ወደ ሲኦል ነው፤
6የቀና የሕይወትን መንገድ አታገኝም፤ በአካሄድዋ የተቅበዘበዘች ናት፥ የሚታወቅም አይደለም።
7አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፥ ከአፌም ቃል አትራቁ።
8መንገድህን ከእርስዋ አርቅ፥ ወደ ቤትዋም ደጅ አትቅረብ፥
9ክብርህ ለሌላ እንዳትሰጥ፥ ዕድሜህም ለጨካኝ፤
10ሌሎች ከሀብትህ እንዳይጠግቡ፥ ድካምህም በባዕድ ሰው ቤት እንዳይሆን።
11በመጨረሻም ሥጋህና ሰውነትህ በጠፋ ጊዜ ታለቅሳለህ፥
12ትላለህም። እንዴት ትምህርትን ጠላሁ፥ ልቤም ዘለፋን ናቀ!
13የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፥ ጆሮቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም።
14በማኅበርና በጉባኤ መካከል ወደ ክፉ ሁሉ ለመድረስ ጥቂት ቀረኝ።
15ከጕድጓድህ ውኃ፥ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ።
16ምንጮችህ ወደ ሜዳ፥ ወንዞችህ ወደ አደባባይ፥ ይፈስሳሉን?
17ለአንተ ብቻ ይሁኑ፥ ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ።
18ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፤ ከጕብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ።
19እንደ ተወደደች ዋላ እንደ ተዋበችም ሚዳቋ፥ ጡትዋ ሁልጊዜ ታርካህ፥ በፍቅርዋም ሁልጊዜ ጥገብ።
20ልጄ ሆይ፥ ስለ ምን ጋለሞታ ሴት ትወድዳለህ? የሌላይቱንስ ብብት ለምን ታቅፋለህ?
21የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና፥ አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና።
22ኃጥኣንን ኃጢአቱ ታጠምደዋለች፥ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል።
23አልተቀጣምና እርሱ ይሞታል፤ በስንፍናውም ብዛት ይስታል።