English

ምዕራፍ 6

1ልጄ ሆይ፥ ለጎረቤትህ ዋስ ብትሆን፥ ስለ ሌላ ሰው እጅህን አጋና ብትመታ፥
2በአፍህ ቃል ተጠመድህ፤ በአፍህ ቃል ተያዝህ።
3ልጄ ሆይ፥ ይህን አድርግ ራስህንም አድን፥ በጎረቤትህ እጅ ወድቀሃልና፤ ፈጥነህ ሂድ፥ ጎረቤትህንም ነዝንዘው።
4ለዓይንህ እንቅልፍን ለሽፋሽፍቶችህም እንጕልቻን አትስጥ፥
5እንደ ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ፥ እንደ ወፍም ከአጥማጅ እጅ ትድን ዘንድ።
6አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን።
7አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት
8መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች።
9አንተ ታካች፥ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ?
10ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂት ታንቀላፋለህ፥ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤
11እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።
12ምናምንቴ ሰው የበደለኛም ልጅ በጠማማ አፍ ይሄዳል፤
13በዓይኑ ይጠቅሳል፥ በእግሩ ይናገራል፥ በጣቱ ያስተምራል፤
14ጠማማነት በልቡ አለ፥ ሁልጊዜም ክፋትን ያስባል፤ ጠብንም ይዘራል።
15ስለዚህ ጥፋቱ ድንገት ይደርስበታል፤ ድንገት ይደቅቃል፥ ፈውስም ከቶ የለውም።
16እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤
17ትዕቢተኛ ዓይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥
18ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥
19በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።
20ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፥ የእናትህንም ሕግ አትተው፤
21ሁልጊዜም በልብህ አኑረው፥ በአንገትህም እሰረው።
22ስትሄድም ይመራሃል፤ ስትተኛ ይጠብቅሃል፤ ስትነሣ ያነጋግርሃል።
23ትእዛዝ መብራት፥ ሕግም ብርሃን ነውና፥ የተግሣጽም ዘለፋ የሕይወት መንገድ ነውና፥
24ከክፉ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ፥ ከሌላይቱም ሴት ምላስ ጥፍጥነት።
25ውበትዋን በልብህ አትመኘው፤ ሽፋሽፍትዋም አያጥምድህ።
26የጋለሞታ ዋጋ እስከ አንዲት እንጀራ ነው፤ አመንዝራም ሴት የሰውን ሕይወት ታጠምዳለች።
27በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፥ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?
28በፍም ላይ የሚሄድ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?
29ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም።
30ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም፤
31ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ በቤቱም ያለውን ሁሉ ይሰጣል።
32ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮው የጐደለ ነው፤ እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል።
33ቍስልንና ውርደትን ያገኛል፥ ስድቡም አይደመሰስም።
34ቅንዓት ለሰው የቍጣ ትኵሳት ነውና፥ በበቀል ቀን አይራራለትምና።
35እርሱም ምንም ካሣ አይቀበልም፥ ስጦታም ብታበዛለት አይታረቅም።