English

ምዕራፍ 8

1በውኑ ጥበብ አትጮኽምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን አትሰጥምን?
2በኮረብታ ላይ በመንገድ አጠገብ በጎዳና መካከል ትቆማለች።
3በበሩ አጠገብ በከተማይቱም መግቢያ፥ በደጁ መግቢያ ትጮኻለች።
4እናንተ ሰዎች፥ እናንተን እጠራለሁ፥ ድምፄም ወደ ሰዎች ልጆች ነው።
5እናንተ አላዋቂዎች፥ ብልሃትን አስተውሉ፤ እናንተም ሰነፎች ጥበብን በልባችሁ ያዙ።
6የከበረች ነገርን እናገራለሁና ስሙ፤ ከንፈሮቼም ቅን ነገርን ለመናገር ይከፈታሉ።
7አፌ እውነትን ይናገራልና፥ ከንፈሮቼም ክፋትን ይጸየፋሉ።
8የአፌ ቃላት ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤ ጠማማ ዘወርዋራም አይደሉም።
9እነርሱ በሚያስተውሉ ዘንድ የቀኑ ናቸው፥ እውቀትንም ካገኙአት ሰዎች ጋር የተስማሙ ናቸው።
10ተግሣጼን እንጂ ብርን አትቀበሉ፥ ከምዝምዝ ወርቅም ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ።
11ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ትበልጣለችና የከበረ ነገር ሁሉ አይተካከላትም።
12እኔ ጥበብ በብልሃት ተቀምጫለሁ፥ እውቀትንም ጥንቃቄንም አግኝቻለሁ።
13እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን ይጠላል፤ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም አፍ እጠላለሁ።
14ምክርና መልካም ጥበብ የእኔ ነው፤ ማስተዋል እኔ ነኝ፥ ብርታትም አለኝ።
15ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፥ ሹማምቶችም የቀናውን ነገር ይደነግጋሉ።
16አለቆች በእኔ ያዝዛሉ፥ ክቡራንና የምድር ፈራጆችም ሁሉ።
17እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል።
18ብልጥግናና ክብር በእኔ ዘንድ ነው፥ ብዙ ሀብትና ጽድቅም።
19ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል፥ ቡቃያዬም ከተመረጠች ብር።
20እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፥ በፍርድም ጎዳና መካከል፥
21ለሚወድዱኝ ርስት አወርሳቸው ዘንድ ቤተ መዛግብታቸውንም እሞላ ዘንድ።
22እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ።
23ከጥንቱ ከዘላለም ጀምሮ ተሾምሁ፤ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ።
24ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ።
25ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፥
26ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር፤ የመጀመሪያውን የዓለም አፈር።
27ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፥
28ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥
29ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥
30የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፥
31ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ።
32አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፤ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው።
33ትምህርቴን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸል አትበሉትም።
34የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ።
35እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና። ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛልና።
36እኔን ያጣ ግን ራሱን ይጐዳል፤ የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።