English

ምዕራፍ 13

1እነሆም፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር።
2በመሠዊያውም ላይ። መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ።
3በዚያም ቀን። እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው፤ እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፥ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል ብሎ ምልክት ሰጠ።
4ንጉሡም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ኢዮርብዓም እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ። ያዙት አለ። በእርሱም ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፥ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም።
5የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፥ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ።
6ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፥ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፥ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እንደ ቀድሞም ሆነች።
7ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና እንጀራም ብላ፥ በረከትም እሰጥሃለሁ አለው።
8የእግዚአብሔርም ሰው ንጉሡን። የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፥ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤
9እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና አለው።
10በሌላም መንገድ ሄደ፥ ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ አልተመለሰም።
11በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ይቀመጥ ነበር፤ ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ ሁሉ ነገሩት ደግሞም ለንጉሡ የተናገረውን ቃል ሁሉ ለአባታቸው ነገሩት።
12አባታቸውም። በማናቸው መንገድ ሄደ? አላቸው። ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ አመለከቱት።
13ልጆቹንም። አህያውን ጫኑልኝ አላቸው፤ አህያውንም በጫኑለት ጊዜ ተቀመጠበት።
14ከእግዚአብሔርም ሰው በኋላ ሄደ፤ በአድባርም ዛፍ በታች ተቀምጦ አገኘውና። ከይሁዳ የመጣህ የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
15እርሱም። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ እንጀራም ብላ አለው።
16እርሱም። ከአንተ ጋር እመለስና እገባ ዘንድ አይቻለኝም፤ በዚህም ስፍራ ከአንተ ጋር እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤
17በዚያ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ተብሎልኛልና አለ።
18እርሱም። እኔ ደግሞ እንደ አንተ ነቢይ ነኝ፤ መልአክም። እንጀራ ይበላ ዘንድ ውኃም ይጠጣ ዘንድ ከአንተ ጋር ወደ ቤትህ መልሰው ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተናገረኝ አለው። ዋሽቶም ተናገረው።
19ከእርሱም ጋር ተመለሰ፥ በቤቱም እንጀራ በላ፥ ውኃም ጠጣ።
20በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ መለሰው ነቢይ መጣ፤
21ከይሁዳም ወደ መጣው ወደ እግዚአብሔር ሰው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ዐምፀሃልና፥ አምላክህም እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥
22ተመልሰህም። እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይደርስም ብሎ ጮኸ።
23እንጀራም ከበላ፥ ውኃም ከጠጣ በኋላ አህያውን ጫነለት።
24ተመልሶም በሄደ ጊዜ በመንገዱ ላይ አንበሳ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋድሞ ነበር፥ አህያውም በእርሱ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ አንበሳውም ደግሞ በሬሳው አጠገብ ቆሞ ነበር።
25እነሆም፥ መንገድ አላፊ ሰዎች ሬሳው በመንገዱ ወድቆ አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆሞ አዩ መጥተውም ሽማግሌው ነቢይ ተቀምጦባት በነበረው ከተማ አወሩ።
26ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ያን በሰማ ጊዜ። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ያመፀ ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል፥ እግዚአብሔር ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ሰብሮም ገድሎታል አለ።
27ልጆቹንም። አህያ ጫኑልኝ አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት።
28ሄደም፥ ሬሳውም በመንገድ ወድቆ፥ በሬሳውም አጠገብ አህያውና አንበሳው ቆመው፥ አንበሳው ሬሳውን ሳይበላው፥ አህያውንም ሳይሰብረው አገኘ።
29ነቢዩም የእግዚአብሔርን ሰው ሬሳ አነሣ፥ በአህያውም ላይ ጭኖ መለሰው፤ ያለቅስለትና ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው ይዞት መጣ።
30ሬሳውንም በገዛ መቃብሩ አኖረው፤ ዋይ ዋይ ወንድሜ ሆይ እያሉ አለቀሱለት።
31ከቀበረውም በኋላ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤
32በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ፥ በሰማርያም ከተሞች ውስጥ ባሉ በኮረብታዎቹ መስገጃዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል የጮኸው ነገር በእውነት ይደርሳልና።
33ከዚህም በኋላ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገድ አልተመለሰም፥ ነገር ግን ለኮረብታዎቹ መስገጃዎች አብልጦ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ፤ የሚወድደውንም ሁሉ ይቀድስ ነበር፥ እርሱም ለኮርብታዎቹ መስገጃዎች ካህን ይሆን ነበር።
34እስኪፈርስም ከምድርም እስኪጠፋ ድረስ ይህ ነገር ለኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት ሆነ።