ምዕራፍ 14
1በዚያም ወራት የኢዮርብዓም ልጅ አብያ ታመመ።
2ኢዮርብዓምም ሚስቱን። ተነሺ፥ የኢዮርብዓምም ሚስት እንደ ሆንሽ እንዳትታወቂ ልብስሽን ለውጪና ወደ ሴሎ ሂጂ፤ እነሆ፥ በዚህ ሕዝብ ላይ እንድነግሥ የነገረኝ ነቢዩ አኪያ በዚያ አለ።
3በእጅሽም አሥር እንጀራና እንጎቻዎች አንድም ምንቸት ማር ይዘሽ ወደ እርሱ ሂጂ፤ በልጁም የሚሆነውን ይነግርሻል አላት።
4የኢዮርብዓምም ሚስት እንዲሁ አደረገች፥ ተነሥታም ወደ ሴሎ ሄደች፤ ወደ አኪያም ቤት መጣች። አኪያም ስለ መሸምገሉ ዓይኖቹ ፈዝዘው ነበርና፤ ማየት አልቻለም።
5እግዚአብሔርም አኪያን። እነሆ፥ ስለ ታመመው ልጅዋ ትጠይቅህ ዘንድ የኢዮርብዓም ሚስት ትመጣለች፤ ሌላ ሴትም መስላ ተሰውራለችና በገባች ጊዜ እንዲህና እንዲህ በላት አለው።
6እርስዋም በደጅ ስትገባ አኪያ የእግርዋን ኮቴ ሰማ፥ እንዲህም አለ። የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ፥ ግቢ፤ ስለ ምንስ ሌላ ሴት መሰልሽ? እኔም ብርቱ ወሬ ይዤ ተልኬልሻለሁ።
7ሂጂ፥ ለኢዮርብዓምም እንዲህ በዪው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከሕዝብ መካከል ለይቼ ከፍ አድርጌህ ነበር፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌህ ነበር፥
8ከዳዊትም ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ሰጥቼህ ነበር፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ እንደ ተከተለኝ፥ በፊቴም ቅን ነገር ብቻ እንዳደረገ፥ ትእዛዜንም እንደ ጠበቀ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም።
9ከአንተም አስቀድመው ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሠራህ፤ ታስቈጣኝም ዘንድ ሄደህ ሌሎችን አማልክትና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች አደረግህ፥ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ።
10ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ መከራ አመጣለሁ፥ ከኢዮርብአምም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ እቈርጣለሁ፤ ሰውም ፋንድያን እስኪጠፋ ድረስ እንደሚጠርግ እኔ የኢዮርብዓምን ቤት ፈጽሜ እጠርጋለሁ።
11ከኢዮርብዓምም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።
12እንግዲህ ተነሥተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እግርሽም ወደ ከተማ በገባ ጊዜ ልጁ ይሞታል።
13እስራኤልም ሁሉ ያለቅሱለታል፥ ይቀብሩትማል፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ በኢዮርብዓም ቤት በዚህ ልጅ መልካም ነገር ተገኝቶበታልና ከኢዮርብዓም እርሱ ብቻ ይቀበራል።
14እግዚአብሔርም ደግሞ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ያስነሣል፤ እርሱም በዚያ ዘመን የኢዮርብዓምን ቤት ያጠፋል።
15በዚያ ጊዜም ሸምበቆ በውኃ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ እግዚአብሔር እንዲሁ እስራኤልን ይመታል፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ የማምለኪያ ዐፀድ ተክለዋልና ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላል፥ በወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል።
16ስለ በደለውና እስራኤልንም ስላሳተበት ስለ ኢዮርብዓም ኃጢአት እስራኤልን ይጥላል።
17የኢዮርብዓምም ሚስት ተነሥታ ሄደች፥ ወደ ቴርሳ መጣች፤ ወደ ቤቱም መድረክ በገባች ጊዜ ልጁ ሞተ።
18በባሪያውም በነቢዩ በአኪያ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስራኤል ሁሉ ቀበሩት አለቀሱለትም።
19የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ እንዴት እንደ ተዋጋ፥ እንዴትም እንደ ነገሠ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
20ኢዮርብዓምም የነገሠበት ዘመን ሀያ ሁለት ዓመት ነበረ፤ ከአባቶቹም ጋር አንቀላፋ፥ ልጁም ናዳብ በፋንታው ነገሠ።
21የሰሎሞንም ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ ሮብዓምም ንጉሥ በሆነ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጉልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም ናዕማ ነበረ፤ እርስዋም አሞናዊት ነበረች።
22ይሁዳም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ፤ አባቶቻቸውም ከሠሩት ሁሉ ይልቅ አብዝተው በሠሩት ኃጢአት አስቈጡት።
23እነርሱም ደግሞ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ ቅጠሉ ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች መስገጃዎችንና ሐውልቶችን የማምለኪያ ዐፀዶችንም ለራሳቸው ሠሩ።
24በምድርም ውስጥ ሰዶማውያን ነበሩ፤ ከእስራኤልም ልጆች ፊት እግዚአብሔር ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኵሰት ሁሉ ያደርጉ ነበር።
25ሮብዓምም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ መጣ።
26የእግዚአብሔርም ቤት መዛግብትንና የንጉሥ ቤት መዛግብትን ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ሰሎሞንም የሠራውን የወርቁን ጋሻ ሁሉ ወሰደ።
27ንጉሡም ሮብዓም በፋንታው የናስ ጋሾችን ሠራ፥ የንጉሥንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቆች እጅ አኖራቸው።
28ንጉሡም ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲገባ ዘበኞች ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር።
29የቀረውም የሮብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
30በዘመኑም ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ሰልፍ ነበረ።
31ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም አብያም በፋንታው ነገሠ። a