ምዕራፍ 5
1የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት በዘመኑ ሁሉ ወዳጅ ስለ ነበረ፥ ሰሎሞን በአባቱ ፋንታ ንጉሥ ለመሆን እንደ ተቀባ ሰምቶ ባሪያዎቹን ወደ ሰሎሞን ሰደደ።
2ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ ብሎ ላከ።
3እግዚአብሔር ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ በዙሪያው ስለ ነበረ ሰልፍ አባቴ ዳዊት የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት እንዳልቻለ አንተ ታውቃለህ።
4አሁንም አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ካሉት ዕረፍት ሰጥቶኛል፤ ጠላትም ክፉም ነገር የለብኝም።
5እነሆም፥ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት። በአንተ ፋንታ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል ብሎ እንደ ነገረው፥ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ አስባለሁ።
6አሁንም ከወገኔ እንደ ሲዶናውያን እንጨት መቈረጥ የሚያውቅ እንደሌለ ታውቃለህና የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ይቈርጡልኝ ዘንድ ባሪያዎችህን እዘዝ፤ ባሪያዎቼም ከባሪያዎችህ ጋር ይሁኑ፤ የባሪያዎችህንም ዋጋ እንደ ተናገርኸው ሁሉ እሰጥሃለሁ።
7ኪራምም የሰሎሞንን ቃል ሰምቶ እጅግ ደስ አለውና። በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ እግዚአብሔር ዛሬ ይመስገን አለ።
8ኪራምም። የላክህብኝን ሁሉ ሰማሁ፤ ስለ ዝግባውና ስለ ጥዱ እንጨት ፈቃድህን ሁሉ አደርጋለሁ።
9ባሪያዎቼ ከሊባኖስ ወደ ባሕር ይጐትቱታል፤ እኔም በታንኳ አድርጌ በባሕር ላይ እያንሳፈፍሁ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ ድረስ አደርስልሃለሁ፥ በዚያም እፈታዋለሁ፥ አንተም ከዚያ ታስወስደዋለህ፤ አንተም ፈቃዴን ታደርጋለህ፤ ለቤቴም ቀለብ የሚሆነውን ትሰጠኛለህ ብሎ ወደ ሰሎሞን ላከ።
10እንዲሁም ኪራም የዝግባውንና የጥዱን እንጨት እንደሚሻው ያህል ሁሉ ለሰሎሞን ይሰጠው ነበር።
11ሰሎሞንም ለኪራም ስለ ቤቱ ቀለብ ሀያ ሺ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ሀያ ኮርም ጥሩ ዘይት ይሰጠው ነበር፤ ሰሎሞንም ለኪራም በየዓመቱ ይህን ይሰጥ ነበር።
12እግዚአብሔርም እንደ ነገረው ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞንም መካከል ሰላም ነበረ፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን ተጋቡ።
13ሰሎሞንም ከእስራኤል ሁሉ ገባሮቹን መርጦ አወጣ፤ የገባሮቹም ቍጥር ሠላሳ ሺህ ሰዎች ነበረ።
14በየወሩም እያከታተለ ወደ ሊባኖስ አሥር አሥር ሺህ ይሰድድ ነበር፤ አንድ ወርም በሊባኖስ ሁለት ወርም በቤታቸው ይቀመጡ ነበር። አዶኒራምም አስገባሪ ነበረ።
15ሰሎሞንም ሰባ ሺህ ተሸካሚዎች፥ ሰማንያ ሺህም በተራራው ላይ የሚጠርቡ ጠራቢዎች ነበሩት።
16ይኸውም በሠራተኛው ሕዝብ ላይ ከተሾሙት ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ሌላ ነው።
17ንጉሡም ታላላቅ ምርጥ ምርጥ ድንጋዮችን ይቈፍሩና ይጠርቡ ዘንድ ለቤቱም መሠረት ይረበርቡት ዘንድ አዘዘ።
18የሰሎሞንና የኪራምም አናጢዎች ጌባላውያንም ወቀሩአቸው፥ ቤቱንም ለመሥራት እንጨቱንና ድንጋዮቹን አዘጋጁ።