English

ምዕራፍ 6

1የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ።
2ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር የሠራው ቤት ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ።
3በመቅደሱም ፊት ወለል ነበረ፤ ርዝመቱም እንደ መቅደሱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ከቤቱ ወደፊት አሥር ክንድ ነበረ።
4ለቤቱም በዓይነ ርግብ የተዘጉ መስኮቶች አደረገ።
5በቤቱም ግንብ ዙሪያ፥ በመቅደሱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግንብ ዙሪያ፥ ደርብ ሠራ፥ በዙሪያውም ጓዳዎች አደረገ።
6የታችኛውም ደርብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ የመካከለኛው ደርብ ወርዱ ስድስት ክንድ፥ የሦስተኛውም ደርብ ወርዱ ሰባት ክንድ ነበረ። ሰረገሎቹ በቤቱ ግንብ ውስጥ እንዳይገቡ ከቤቱ ግንብ ውጭ ዓረፍቶች አደረገ።
7ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ፤ በተሠራም ጊዜ መራጃና መጥረቢያ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም።
8የታችኛውም ደርብ ጓዳዎች በር በቤቱ ቀኝ አጠገብ ነበረ። ከዚያም ወደ መካከለኛው ደርብ፥ ከመካከለኛውም ወደ ሦስተኛው ደርብ በመውጫ ያስወጣ ነበር።
9ቤቱንም ሠርቶ ፈጸመው፤ በዝግባው ሰረገሎችና ሳንቃዎች ከደነው።
10በቤቱም ሁሉ ዙሪያ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆነ ደርቦች ሠራ፤ ከቤቱም ጋር በዝግባ እንጨት አጋጠማቸው።
11የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን መጣ እንዲህ ሲል።
12ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት በሥርዓቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስበትም ዘንድ ትእዛዜን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ።
13በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም።
14ሰሎሞንም ቤቱን ሠራው፥ ፈጸመውም።
15የቤቱንም ግንብ ውስጡን በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ ከቤቱም መሠረት ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ ውስጡን በእንጨት ለበጠው፤ ደግሞም የቤቱን ወለል በጥድ እንጨት ከደነው።
16በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን ይሆን ዘንድ ኋለኛውን ሀያውን ክንድ በዝግባ እንጨት ጋረደው።
17በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ያለውም መቅደስ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበረ።
18የቤቱንም ውስጥ በተጐበጐበና በፈነዳ አበባ በተቀረጸ ዝግባ ለበጠው፤ ሁሉም ዝግባ ነበረ፤ ድንጋዩም አልታየም ነበር።
19በዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ያኖር ዘንድ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን አበጀ።
20የቅድስተ ቅዱሳንም ርዝመት ሀያ ክንድ፥ ስፋቱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው።
21በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ከዝግባ የተሠራ መሠዊያ አደረገ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው።
22ቤቱንም ሁሉ ፈጽሞ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት የነበረውን መሠዊያ ሁሉ በወርቅ ለበጠው።
23በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ።
24የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስክ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ አሥር ክንድ ነበረ።
25ሁለተኛውም ኪሩብ አሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበረ።
26የአንዱ ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ።
27ኪሩቤልንም በውስጠኛው ቤት አኖራቸው፤ የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፥ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር።
28ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው።
29በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ።
30የቤቱንም ወለል በውስጥና በውጭ በወርቅ ለበጠ።
31ለቅዱስተ ቅዱሳኑም መግቢያ ከወይራ እንጨት ደጆች ሠራ፤ መድረኩንና መቃኖቹን ደፉንም አምስት ማዕዘን አደረገ።
32ሁለቱንም ደጆች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፥ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልናና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጣቸው።
33እንዲሁም ለመቅደሱ መግቢያ ከወይራ እንጨት አራት ማዕዘን መቃን አደረገ።
34ሁለቱንም ደጆች ከጥድ እንጨት ሠራ፤ አንዱ ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፥ ሁለተኛውም ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ።
35የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው።
36የውስጠኛውንም አደባባይ ቅጥር ሦስቱን ተራ በተጠረበ ድንጋይ፥ አንዱንም ተራ በዝግባ ሳንቃ ሠራው።
37በአራተኛው ዓመት ዚፍ በሚባል ወር የእግዚአብሔር ቤት ተመሠረተ።
38በአሥራ አንደኛውም ዓመት ቡል በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱ እንደ ክፍሎቹና እንደ ሥርዓቱ ሁሉ ተጨረሰ። በሰባትም ዓመት ውስጥ ሠራው። a