ምዕራፍ 26
1የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የአሥራ ስድስት ዓመት ጕልማሳ የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት።
2ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ከአንቀላፋ በኋላ ዖዝያን ኤላትን ሠራ፥ ወደ ይሁዳም መለሳት።
3ዖዝያንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስድስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
4አባቱም አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
5እግዚአብሔርንም መፍራት ባስተማረ በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልብ አደረገ፤ እግዚአብሔርንም በፈለገ ጊዜ እግዚአብሔር ነገሩን አከናወነለት።
6ወጥቶም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ የጌትንና የየብናን የአዞጦንንም ቅጥር አፈረሰ፤ በአዛጦንና በፍልስጥኤማውያንም አገር ከተሞችን ሠራ።
7እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያንና በጉርበኣል በሚኖሩ ዓረባውያን በምዑናውያንም ላይ ረዳው።
8አሞናውያንም ለዖዝያን ገበሩ፤ እጅግም በርትቶ ነበርና ዝናው እስከ ግብጽ መግቢያ ድረስ ተሰማ።
9ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በርና በሸለቆው በር ቅጥሩም በዞረበት ማዕዘን አጠገብ ግንቦችን ሠርቶ መሸጋቸው።
10ብዙም እንስሶች ነበሩበትና በምድረ በዳና በቈላው በደጋውም ግንብ ሠራ፥ ብዙ ጕድጓድም ማሰ፤ ደግሞም እርሻ ይወድድ ነበርና በተራራማውና በፍሬያማው ስፍራ አራሾችና አትክልተኞች ነበሩት።
11ደግሞም ለዖዝያን በሠራዊት ውስጥ ሰልፈኞች ነበሩት፤ በንጉሡ አለቃ በሐናንያ ትእዛዝ በአለቃው በመዕሤያና በጸሐፊው በይዒኤል እጅ እንደ ተቈጠሩ ወደ ሰልፍ በየቍጥራቸው ይወጡ ነበር።
12የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች የጽኑዓን ኃያላኑ ቍጥር ሁሉ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበረ።
13ንጉሡንም በጠላቱ ላይ ያግዝ ዘንድ፥ በታላቅ ኃይል ወደ ሰልፍ የሚወጣ፥ ከእጃቸው በታች የነበረ ሠራዊት ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበረ።
14ዖዝያንም ለጭፍራው ሁሉ ጋሻና ጦር፥ ራስ ቍርና ጥሩር፥ ቀስትና የሚወነጭፉትን ድንጋይ አዘጋጀላቸው።
15በኢየሩሳሌምም በብልሃተኞች እጅ የተሠሩትን፥ በግንብና በቅጥር ላይ የሚኖሩትን፥ ፍላጻና መርግ የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አደረገ፤ እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና ዝናው እስከ ሩቅ ድረስ ተሰማ።
16ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፥ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፤ ወደ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ።
17ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ገቡ።
18ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ። ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን የተቀደሱት የአሮን ልጆች የካህናቱ ሹመት ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ ለአንተ አይገባህም፤ በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከአምላክህም ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብር አይሆንልህም አሉት።
19ዖዝያንም ተቈጣ፤ የሚያጥንበትም ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቈጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ።
20ታላቁም ካህን ዓዛርያስ ካህናቱም ሁሉ ተመለከቱት፥ እነሆም፥ በግምባሩ ላይ ለምጽ ነበረ፤ ፈጥነውም አባርረሩት፥ እርሱም ደግሞ እግዚአብሔር ቀሥፎት ነበርና ይወጣ ዘንድ ቸኰለ።
21ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻምም ሆኖ ከእግዚአብሔር ቤት ተቈርጦአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር፤ ልጁም ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ ሆኖ በምድሩ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር።
22የቀረውንም የፊተኛውንና የኋለኛውን የዖዝያንን ነገር ነቢዩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ጽፎታል።
23ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ ለምጻም ነው ብለውም ከአባቶቹ ጋር በነገሥታቱ መቃብር እርሻ ውስጥ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።