English

ምዕራፍ 27

1ኢዮአታምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ኢየሩሳ ትባል ነበር።
2አባቱም ዖዝያን እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር መቅደስ አልገባም፤ ሕዝቡም ገና ይበድል ነበር።
3የእግዚአብሔርን ቤት የላይኛውን በር ሠራ፥ በዖፌልም ቅጥር ላይ እጅግ ሠራ።
4በተራራማውም በይሁዳ አገር ላይ ከተሞችን ሠራ፥ በዱር ስፍራዎችም አምባዎችንና ግንቦችን ሠራ።
5ከአሞንም ልጆች ንጉሥ ጋር ተዋጋ አሸነፋቸውም። በዚያም ዓመት የአሞን ልጆች መቶ መክሊት ብር፥ አሥር ሺህም የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ አሥር ሺህም የቆሬስ መሥፈሪያ ገብስ ሰጡት። እንዲሁም ደግሞ የአሞን ልጆች በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ሰጡት።
6ኢዮአታምም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መንገዱን አቅንቶአልና በረታ።
7የቀረውም የኢዮአታም ነገር፥ ሰልፉም ሁሉ፥ ሥራውም፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
8መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ።
9ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አካዝ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።