English

ምዕራፍ 21

1እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሣራን አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት።
2ሣራም ፀነሰች፥ እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት።
3አብርሃምም የተወለደለትን ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው።
4አብርሃምም ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር እንዳዘዘው በስምንተኛ ቀን ገረዘው።
5አብርሃምም ልጁ ይስሐቅ በተወለደለት ጊዜ የመቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ።
6ሣራም። እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል፤ ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች።
7ደግሞም። ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው? በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና አለች።
8ሕፃኑም አደገ፥ ጡትንም ከመጥባት ተቋረጠ፤ አብርሃምም ይስሐቅን ጡት ባስጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣን አደረገ።
9ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው።
10አብርሃምንም። ይህችን ባሪያ ከነልጅዋ አሳድድ፤ የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና አለችው።
11ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት።
12እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ስለ ባሪያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፤ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ፤ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና።
13የባሪያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ፥ ዘርህ ነውና።
14አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፥ እንጀራንም ወሰደ፥ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፥ ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት፤ እርስዋም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች።
15ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፤ ብላቴናውንም ከአንድ ቍጥቋጦ በታች ጣለችው፤
16እርስዋም ሄደች። ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች።
17እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት። አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ።
18ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፤ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።
19እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጕድጓድንም አየች፤ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች።
20እግዚአብሔርም ከብላቴናው ጋር ነበረ፤ አደገም፥ በምድረ በዳም ተቀመጠ፥ ቀስተኛም ሆነ።
21በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት።
22በዚያም ዘመን አቢሜሌክ ከሙሽራው ወዳጅ ከአኮዘትና ከሠራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር አብርሃምን አለው። በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤
23አሁንም በእኔም በልጄም በልጅ ልጄም ክፉ እንዳታደርግብኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ፤ ነገር ግን ለአንተ ቸርነትን እንዳደረግሁ አንተም ለእኔ ለተቀመጥህባትም ምድር ቸርነትን ታደርጋለህ።
24አብርሃምም። እኔ እምላለሁ አለ።
25አቢሜሌክንም ባሪያዎቹ በነጠቁት በውኃ ጕድጓድ ምክንያት አብርሃም ወቀሰው።
26አቢሜሌክም አለ። ይህን ነገር ያደረገውን አላወቅሁም፤ አንተም ደግሞ ምንም አልነገርኸኝም፥ እኔም ከዛሬ በቀር አልሰማሁም።
27አብርሃምም በጎችንና ላሞችን አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ።
28አብርሃምም ሰባት ቄቦች በጎችን ለብቻቸው አቆመ።
29አቢሜሌክም አብርሃምን። ለብቻቸው ያቆምሃቸው እነዚህ ሰባት ቄቦች በጎች ምንድር ናቸው? አለው።
30እርሱም። እኔ ይህችን የውኃ ጕድጓድ እንደቆፈርሁ ምስክር ይሆንልኝ ዘንድ እነዚህን ሰባት ቄቦች በጎች ከእጄ ትወስዳለህ አለው።
31ስለዚህ የዚያን ስፍራ ስም ቤርሳቤህ ብሎ ጠራው፤ ከዚያ ሁለቱ ተማምለዋልና።
32በቤርሳቤህም ቃል ኪዳንን አደረጉ። አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱ አለቃ ፊኮልም ተነሥተው ወደ ፍልስጥኤም ምድር ተመለሱ።
33አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍን ተከለ፤ በዚያም የዘላለሙን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ።
34አብርሃምም በፍልስጥኤም ምድር ብዙ ቀን እንግዳ ሆኖ ተቀመጠ።