ምዕራፍ 22
1ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው። አብርሃም ሆይ። አብርሃምም። እነሆ፥ አለሁ አለ።
2የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ።
3አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፥ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሕቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ እንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ።
4በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ዓይኑን አነሣና ቦታውን ከሩቅ አየ።
5አብርሃምም ሎሌዎቹን አላቸው። አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ሄደን እንሰግዳለን፥ ወደ እናንተም እንመለሳለን።
6አብርሃምም የመሥዋዕቱን እንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዋውን በእጁ ያዘ፥ ሁለቱም አብረው ሄዱ።
7ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን ተናገረው። አባቴ ሆይ አለ። እርሱም። እነሆኝ፥ ልጄ አለው። እሳቱና እንጨቱ ይኸው አለ፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት ነው? አለ።
8አብርሃምም። ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ።
9እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያውን ሠራ፥ እንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው።
10አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ።
11የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው፤
12እርሱም። እነሆኝ አለ። እርሱም። በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ።
13አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው።
14አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል።
15የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፥
16እንዲህም አለው። እግዚአብሔር። በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና
17በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤
18የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና።
19አብርሃምም ወደ ብላቴኖቹ ተመለሰ፥ ተነሥተውም ወደ ቤርሳቤህ አብረው ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ተቀመጠ።
20ይህም ከሆነ በኋልላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረ። እነሆ፥ ሚልካ ደግሞ ለወንድምህ ለናኮር ልጆችን ወለደች፤
21እነርሱም በኵሩ ዑፅ፥ ወንድሙ ቡዝ፥ የአራም አባት ቀሙኤል፥
22ኮዛት፥ ሐዞ፥ ፊልዳሥ፥ የድላፍ፥ ባቱኤል ናቸው።
23ባቱኤልም ርብቃን ወለደ፤ እነዚህን ስምንቱን ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር ወለደች።
24ሬሕማ የሚሉአት ቁባቱ ደግሞ ጥባህን፥ ገአምን፥ ተሐሸን፥ ሞክሳን ወለደች።