ምዕራፍ 31
1ያዕቆብም የላባ ልጆች ያሉትን ነገር። ያዕቆብ ለአባታችን የሆነውን ሁሉ ወሰደ፤ ይህንም ሁሉ ክብር ከአባታችን ከብት አገኘ ሲሉ ሰማ።
2ያዕቆብም የላባን ፊት አየ፥ እነሆም ከእርሱ ጋር እንደ ዱሮው አልሆነም።
3እግዚአብሔርም ያዕቆብን። ወደ አባትህ ምድር ወደ ዘመዶችህም ተመለስ፤ ከአንተም ጋር እሆናለሁ አለው።
4ያዕቆብም ልኮ ራሔልንና ልያን ወደ በጎቹ ስፍራ ወደ ሜዳ ጠራቸው፥
5እንዲህም አላቸው። የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደ ዱሮ እንዳልሆነ አያለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው።
6እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ።
7አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉ ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም።
8ደመወዝህ ዝንጕርጕሮች ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕሮችን ወለዱ፤ ሽመልመሌ መሳዮቹ ደመወዝህ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮችን ወለዱ።
9እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ።
10እንዲህም ሆነ፤ በጎቹ በጎመጁ ጊዜ ዓይኔን አንሥቼ በሕልም አየሁ፤ እነሆም፥ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ነበሩ።
11የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይ አለኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁት።
12እንዲህም አለኝ። ዓይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና።
13ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ።
14ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት። በአባታችን ቤት ለእኛ ድርሻና ርስት በውኑ ቀርቶልናልን?
15እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልና።
16ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ይህ ሁሉ ሀብት ለእኛና ለልጆቻችን ነው፤ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ።
17ያዕቆብም ተነሣ፥ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤
18መንጎቹንም ሁሉ፥ የቤቱንም ዕቃ ሁሉ፥ በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ።
19ላባ ግን በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባትዋን ተራፊም ሰረቀች።
20ያዕቆብም የሶርያውን ሰው ላባን ከድቶ ኮበለለ፥ መኮብለሉንም፥ አልነገረውም።
21እርሱም ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፤ ተነሥቶም ወንዙን ተሻገረ፥ ፊቱንም ወደ ገለዓድ ተራራ አቀና።
22በሦስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ተነገረው።
23ከወንድሞቹም ጋር ሆኖ የሰባት ቀን መንገድ ያህል ተከተለው፥ በገለዓድ ተራራም ላይ ደረሰበት።
24እግዚአብሔርም ወደ ሶርያው ሰው ወደ ላባ በሌሊት ሕልም መጥቶ። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ አለው።
25ላባም ደረሰበት፤ ያዕቆብም ድንኳኑን በተራራው ተክሎ ነበር፤ ላባም ከወንድሞቹ ጋር በገለዓድ ተራራ ድንኳኑን ተከለ።
26ላባም ያዕቆብን አለው። ለምን እንዲህ አደረግህ? ከእኔ ከድተህ ኮበለልህ፥ ልጆቼንም በሰይፍ እንደ ተማረኩ ዓይነት ነዳሃቸው።
27ስለምን በስውር ሸሸህ? ከእኔም ከድተህ ስለምን ኮበለልህ? በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም?
28ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቼን እንድስም ስለ ምን አልፈቀድህልኝም? ይህንም በስንፍና አደረግህ።
29ክፉ አደርግባችሁ ዘንድ ኃይል ነበረኝ፤ ነገር ግን የአባታችሁ አምላክ ትናንት። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ ብሎ ነገረኝ።
30አሁንም የአባትህን ቤት ከናፈቅህ ሂድ፤ ነገር ግን አምላኮቼን ለምን ሰረቅህ?
31ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። ልጆችህን ከእኔ የምትቀማኝ ስለመሰለኝና ስለፈራሁ ይህን አደረግሁ።
32አምላኮችህን የምታገኝበት ሰው ግን እርሱ ይሙት፤ የአንተ የሆነውም በእኔ ዘንድ ይገኝ እንደ ሆነ በወንድሞቻችን ፊት ፈልግ፥ ለአንተም ውሰደው አለ። ራሔል እንደ ሰረቀቻቸው ያዕቆብ አያውቅም ነበርና።
33ላባም ወደ ያዕቆብ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን ወደ ሁለቱም ባሪያዎች ድንኳን ገባ፥ ነገር ግን አላገኘም። ከልያም ድንኳን ወጥቶ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ።
34ራሔልም ተራፊምን ወስዳ ከግመል ኮርቻ በታች ሸሸገች፥ በላዩም ተቀመጠችበት። ላባም ድንኳኑን ሁሉ ፈለገ፥ አንዳችም አላገኘም።
35እርስዋም አባትዋን። በፊትህ ለመቆም ስላልቻልሁ አትቆጣብኝ፤ በሴቶች የሚደርስ ግዳጅ ደርሶብኛልና አለችው። እርሱም ፈለገ፥ ነገር ግን ተራፊምን አላገኘም።
36ያዕቆብም ተቆጣ ላባንም ወቀሰው፤ ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። የበደልሁህ በደል ምንድር ነው? ኃጢአቴስ ምንድር ነው ይህን ያህል ያሳደድኸኝ?
37አሁንም ዕቃዬን ሁሉ በረበርህ፤ ከቤትህስ ዕቃ ሁሉ ምን አገኘህ? እነርሱ በእኛ በሁለታችን መካከል ይፈርዱ ዘንድ በወንድሞቼና በወንድሞችህ ፊት አቅርበው።
38ሀያ ዓመት ሙሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም፤ የመንጎችህንም ጠቦቶች አልበላሁም፤ አውሬ የሰበረውን አላመጣሁልህም ነበር፤
39እኔ ስለ እርሱ እከፍልህ ነበርሁ፤ በቀንም በሌሊትም የተሰረቀውን ከእጄ ትሻው ነበርህ።
40የቀን ሐሩር የሌሊት ቍር ይበላኝ ነበር፥ እንቅልፍም ከዓይኔ ጠፋ።
41እንዲሁ በአንተ ቤት ሀያ ዓመት ነበርሁ አሥራ አራት ዓመት ስለ ሁለቱ ሴቶች ልጆችህ፥ ስድስት ዓመትም ስለ በጎችህ ተገዛሁልህ፤ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለዋወጥኸው።
42የአባቴ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም ፍርሃት ከእኔ ጋር ባይሆንስ ዛሬ ባዶ እጄን በሰደድኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር መከራዬንና የእጆቼን ድካም አየ፥ ትናንትም ገሠጸህ።
43ላባም እንዲህ ብሎ ለያቆብ መለሰለት። ሴቶቹ ልጆች ልጆቼ ናቸው፥ ሕፃናቱም ሕፃናቴ ናቸው፥ መንጎቹም መንጎቼ ናቸው፥ የምታየውም ሁሉ የእኔ ነው፤ ዛሬም በእነዚህ በሴቶች ልጆቼና በወለዱአቸው ልጆቻቸው ላይ ምን ላደርግ ይቻላል?
44አሁንም ና፥ አንተና እኔ ቃል ኪዳን እንጋባ፤ በእኔና በአንተ መካከልም ምስክር ይሁን።
45ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አቆመ።
46ያዕቆብም ወንድሞቹን። ድንጋይ ሰብስቡ አላቸው፤ እነርሱም ድንጋይ ሰብስበው ከመሩ፤ በድንጋዩም ክምር ላይ በሉ።
47ላባም ይጋር ሠሀዱታ ብሎ ጠራት፤ ያዕቆብም ገለዓድ አላት።
48ላባም። ይህች ክምር በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ናት አለ። ስለዚህም ስምዋ ገለዓድ ተባለ፤
49ደግሞም ምጽጳ ተባለ። እኛ በተለያየን ጊዜ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ሆኖ ይጠብቅ ብሎአልና።
50ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም በላያቸው ሚስቶችን ብታገባባቸው ከእኛ ጋር ያለ ሰው የለም፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ምስክር ነው።
51ላባም ያዕቆብን አለው። በእኔና በአንተ መካከል እነሆ ይህች ክምር፥ እነሆም ያቆምኋት ሐውልት፤
52እኔ ወደ አንተ ይህችን ክምር እንዳላልፍ፥ አንተም ለክፋት ወደ እኔ ይህችን ክምርና ይህችን ሐውልት እንዳታልፋት፥ ይህች ክምር ምስክር ናት፥ ይህችም ሐውልት ምስክር ናት።
53የአብርሃም አምላክ የናኮርም አምላክ የአባታቸውም አምላክ በእኛ መካከል ይፍረድ። ያዕቆብም በአባቱ በይስሐቅ ፍርሃት ማለ።
54ያዕቆብም በተራራው ላይ መሥዋዕትን ሠዋ፥ ወንድሞቹንም እንጀራ እንዲበሉ ጠራ፤ እነርሱም እንጀራን በሉ፥ በዚያም በተራራ አደሩ።
55ላባም ማልዶ ተነሥቶ ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቹን ሳመ ባረካቸውም፤ ላባም ተመልሶ ወደ ስፍራው ሄደ።