English

ምዕራፍ 32

1ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት።
2ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ። እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው አለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም መሃናይም ብሎ ጠራው።
3ያዕቆብም ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ወደ ሴይር ምድር ወደ ኤዶም አገር ከፊቱ መልእክተኞችን ላከ፤
4እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። ለጌታዬ ለዔሳው። ባሪያህ ያዕቆብ እንዲህ አለ ብላችሁ ንገሩት። በላባ ዘንድ በስደት ተቀመጥሁ፤ እስከ አሁን ድረስ ቆየሁ፤
5ላሞችንም አህዮችንም በጎችን ወንዶች ባሪያዎችንም ሴቶች ባሪያዎችንም አገኘሁ፤ አሁንም በፊትህ ሞገስን አገኝ ዘንድ ለጌታዬ ለማስታወቅ ላክሁ።
6መልእክተኞቹም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት። ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ።
7ያዕቆብም እጅግ ፈርቶ ተጨነቀ፤ ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች መንጎችንም ላሞችንም ግመሎችንም በሁለት ወገን ከፈላቸው፤
8እንዲህም አለ። ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደ ሆነ የቀረው ወገን ያመልጣል።
9ያዕቆብም አለ። የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴም የይስሐቅ አምላክ ሆይ። ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፥ በጎነትንም አደርግልሃለሁ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፤
10ለባሪያህ ከሠራኸው ከምሕረትህና ከእውነትህም ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፥ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ።
11ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና።
12አንተም። በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ ብለህ ነበር።
13በዚያችም ሌሊት ከዚያው አደረ። ከያዘውም ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻን አወጣ፤
14ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሀያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሀያ የበግ አውራዎችን፥
15ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ አሥር በሬ፥ ሀያ እንስት አህያ፥ አሥርም የእህያ ግልገሎችን።
16መንጎቹን በየወገኑ ከፍሎ በባሪያዎቹ እጅ አደረጋቸው፤ ባሪያዎቹንም። በፊቴ እለፉ መንጋውንና መንጋውንም አራርቁት አለ።
17የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው። ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደሆነ። አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? በፊትህ ያለው ይህስ የማን ነው? ብሎ የጠየቀህም እንደ ሆነ፥
18በዚያን ጊዜ አንተ። ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደደው የባሪያህ የያዕቆብ ነው፤ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ነው በለው።
19እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ከመንጎችም በኋላ የሚሄዱትን ሁሉ እንዲሁ ብሎ አዘዘ። ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት፤
20እንዲህም በሉት። እነሆ ባሪያህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው። በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይራራልኛል ፊቱንም አያለሁ ብሎአልና።
21እጅ መንሻው ከእርሱ ቀድሞ አለፈ፤ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት በሰፈር አደረ።
22በዚያች ሌሊትም ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ባሪያዎቹን አሥራ አንዱንም ልጆቹን ወስዶ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ።
23ወሰዳቸውም ወንዙንም አሻገራቸው፥ ከብቱንም ሁሉ አሻገረ።
24ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር።
25እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ ያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ።
26እንዲህም አለው። ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ። እርሱም። ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም አለው።
27እንዲህም አለው። ስምህ ማን ነው? እርሱም። ያዕቆብ ነኝ አለው።
28አለውም። ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና።
29ያዕቆብም። ስምህን ንገረኝ ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? አለው። በዚያም ስፍራ ባረከው።
30ያዕቆብም፦ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል ብሎ ጠራው።
31ጵኒኤልንም ሲያልፍ ፀሐይ ወጣችበት፥ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር።
32ስለዚህም የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ የወርችን ሹልዳ አይበሉም፤ የያዕቆብን ጭን ይዞ የወርችን ሹልዳ አደንዝዞአልና። q ቍ@ 30፤ ጵኒኤል የሚለውን ቃል የግእዝ መጽሐፍ ራእየ እግዚአብሔር ይለዋል። a