English

ምዕራፍ 37

1ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት አገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ።
2የያዕቆብም ትውልድ ይህ ነው። ዮሴፍ የአሥራ ሰባት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር በጎችን ይጠብቅ ነበር፤ እርሱም ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ልጆች ጋር ሳለ ብላቴና ነበረ፤ ዮሴፍም የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው አመጣ።
3እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር፥ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና፤ በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት ።
4ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንዲወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም።
5ዮሴፍም ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እነርሱም እንደ ገና በብዙ ጠሉት።
6እርሱም አላቸው። እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤
7እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና፥ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።
8ወንድሞቹም። በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን? አሉት። እንደ ገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ ይልቁን ጠሉት።
9ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እንዲህም አለ። እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፤ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።
10ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ አባቱም ገሠጸው፥ እንዲህም አለው። ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?
11ወንድሞቹም ቀኑበት አባቱ ግን ነገሩን ይጠብቀው ነበር።
12ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ።
13እስራኤልም ዮሴፍን። ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና አለው። እርሱም። እነሆኝ አለው ።
14እርሱም። ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ አለው። እንዲህም ከኬብሮን ቈላ ሰደደው፥ ወደ ሴኬምም መጣ።
15እነሆም በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውዮውም። ምን ትፈልጋለህ? ብሎ ጠየቀው።
16እርሱም ወንድሞቼን እፈልጋለሁ፤ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ አለ።
17ሰውዮውም። ከዚህ ተነሥተዋል፤ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፥ በዶታይንም አገኛቸው።
18እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ።
19አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው። ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ።
20አሁንም ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው። ክፉ አውሬም በላው እንላለን፤ ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን።
21ሮቤልም ይህን ሰማ፥ ከእጃቸውም አዳነው፥ እንዲህም አለ። ሕይወቱን አናጥፋ።
22ሮቤል። ደም አታፍስሱ፤ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው።
23እንዲህም ሆነ፤ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፤
24ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ።
25እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ፤ ዓይናቸውንም አንሥተው አዩ፥ እነሆም የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ መጡ፤ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን ከርቤም ተጭነው ነበር።
26ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው። ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድር ነው?
27ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና። ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት።
28የምድያም ነጋዶችም አለፉ፤ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጕድጓድ አወጡት፤ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሀያ ብር ሸጡት፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት።
29ሮቤልም ወደ ጕድጓዱ ተመለሰ፥ እነሆም ዮሴፍ በጕድጓድ የለም፤ ልብሱንም ቀደደ።
30ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ። ብላቴናው የለም፤ እንግዲህ እኔ ወዴት እሄዳለሁ? አለ።
31የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፥ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት።
32ብዙ ኅብር ያለበትን ቀሚሱንም ላኩ፥ ወደ አባታቸውም አገቡት፥ እንዲህም አሉት። ይህንን አገኘነ፤ ይህ የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው።
33እርሱም አውቆ። የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል አለ።
34ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ፥ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ።
35ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፤ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ። ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ።
36እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጲጥፋራ ሸጡት።