English

ምዕራፍ 38

1በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ወረደ፥ ስሙን ኤራስ ወደሚሉት ወደ ዓዶሎማዊውም ሰው ገባ።
2ከዚያም ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ አየ፤ ወሰዳትም፥ ወደ እርስዋም ገባ።
3ፀነሰችም ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው።
4ደግሞም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም አውናን ብላ ጠራችው።
5እንደ ገና ደግሞ ወንድ ልጅን ወለደች፥ ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው፤ እርሱንም በወለደች ጊዜ ክዚብ በሚባል አገር ነበረች።
6ይሁዳም ለበኵር ልጁ ለዔር ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው።
7የይሁዳም የበኵር ልጅ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው።
8ይሁዳም አውናን። ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ፥ አግባትም፥ ለወንድምህም ዘርን አቁምለት አለው።
9አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ፤ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈስስው ነበር።
10ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፥ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው።
11ይሁዳም ምራቱን ትዕማርን። ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ አላት፤ እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞት ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባትዋ ቤት ተቀመጠች።
12ከብዙ ዘመንም በኋላ የይሁዳ ሚስት የሴዋ ልጅ ሞተች፤ ይሁዳም ተጽናና፥ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ፥ እርሱም ዓዶሎማዊው ወዳጁም ኤራስ።
13ለትዕማርም። እነሆ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል ብለው ነገሩአት።
14እርስዋም የመበለትነትዋን ልብስ አወለቀች፥ መጎናጸፊያዋንም ወሰደች፥ ተሸፈነችም፥ ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ሴሎም እንደ አደገ ሚስትም እንዳልሆነችው አይታለችና።
15ይሁዳም ባያት ጊዜ ጋለሞታን መሰለችው፤ ፊትዋን ተሸፍና ነበርና።
16ወደ እርስዋም አዘነበለ። እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት፤ እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም። ወደኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ? አለችው።
17የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እሰድድልሻለሁ አላት። እርስዋም። እስክትሰድድልኝ ድረስ መያዣ ትሰጠኛለህን? አለችው።
18እርሱም። ምን መያዣ ልስጥሽ? አላት። እርስዋም። ቀለበትህን፥ አምባርህን፥ በእጅህ ያለውን በትር አለች። እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ጋር ደረሰ፥ እርስዋም ፀነሰችለት።
19እርስዋም ተነሥታ ሄደች፥ መጎናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነትዋን ልብስ ለበሰች።
20ይሁዳም መያዣውን ከሴቲቱ እጅ ይቀበል ዘንድ በወዳጁ በዓዶሎማዊው እጅ የፍየሉን ጠቦት ላከላት፤ እርስዋንም አላገኛትም።
21እርሱም የአገሩን ሰዎች። በኤናይም በመንገድ ዳር ተቀምጣ የነበረች ጋለሞታ ወዴት ናት? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም። በዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉት።
22ወደ ይሁዳም ተመልሶ እንዲህ አለው። አላገኘኋትም፤ የአገሩም ሰዎች ደግሞ። ከዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉኝ።
23ይሁዳም። እኛ መዘበቻ እንዳንሆን ትውሰደው፤ እነሆ የፍየሉን ጠቦት ሰደድሁላት፥ አንተም አላገኘሃትም አለ።
24እንዲህም ሆነ፤ ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ። ምራትህ ትዕማር ሴሰነች፤ ደግሞም በዝሙት እነሆ ፀነሰች ብለው ነገሩት። ይሁዳም። አውጡአትና በእሳት ትቃጠል አለ።
25እርስዋም ባወጡአት ጊዜ ወደ አማትዋ እንዲህ ብላ ላከች። ለዚህ ለባለ ገንዘብ ነው የፀነስሁት፤ ተመልከት፤ ይህ ቀለበት፥ ይህ አምባር፥ ይህ በትር የማን ነው?
26ይሁዳም አወቀ። ከእኔ ይልቅ እርስዋ እውነተኛ ሆነች፤ ልጄን ሴሎምን አልሰጠኋትምና አለ። ደግሞም አላወቃትም።
27በመውለጃዋም ጊዜ እነሆ መንታ ልጆች በሆድዋ ነበሩ።
28ስትወልድም አንዱ እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም ቀይ ፈትል ወስዳ በእጁ አሰረች። ይህ መጀመሪያ ይወጣል አለች።
29እንዲህም ሆነ፤ እጁን በመለሰ ጊዜ እነሆ ወንድሙ ወጣ፤ እርስዋም። ለምን ጥስህ ወጣህ? አለች፤ ስሙንም ፋሬስ ብላ ጠራችው።
30ከእርሱም በኋላ ቀይ ፈትል በእጁ ያለበት ወንድሙ ወጣ፤ ስሙም ዛራ ተባለ።