ምዕራፍ 135
1ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔርን ስም አመስግኑ፤ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥
2በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ፥ በአምላካችን ቤት አደባባይ የምትቆሙ።
3እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ለስሙ ዘምሩ፥ መልካም ነውና፤
4እግዚአብሔር ያዕቆብን ለራሱ፥ እስራኤልንም ለመዝገቡ መርጦታልና፤
5እግዚአብሔር ታላቅ እንደ ሆነ፥ ጌታችንም ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አውቄአለሁና።
6በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ፥ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ።
7ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፤ በዝናብ ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል።
8የግብጽን በኵር ልጆች ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ መታ።
9ግብጽ ሆይ፥ በመካከልሽ በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ ተኣምራትንና ድንቅን ሰደደ።
10ብዙ አሕዛብን መታ፥ ብርቱዎችንም ነገሥታት ገደለ።
11የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ የባሳንንም ንጉሥ ዐግን፥ የከነዓንን መንግሥታት ሁሉ ገደለ፤
12ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ለሕዝቡ ርስት ሰጠ።
13አቤቱ፥ ስምህ ለዘላለም ነው፥ ዝክርህም ለልጅ ልጅ ነው፤
14እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳልና፥ ባሪያዎቹንም ይረዳልና።
15የአሕዛብ ጣዖታት የብርና የወርቅ፥ የሰው እጅ ሥራ ናቸው።
16አፍ አላቸው፥ አይናገሩምም፤ ዓይን አላቸው፥ አያዩምም፤
17ጆሮ አላቸው፥ አይሰሙምም፤ እስትንፋስም በአፋቸው የለም።
18የሚሠሩአቸው ሁሉ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁን።
19የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት። የአሮን ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት፤
20የሌዊ ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት።
21በኢየሩሳሌም የሚያድር እግዚአብሔር ከጽዮን የተባረከ ነው። ሃሌ ሉያ።