English

ምዕራፍ 30

1አቤቱ፥ ተቀብለኸኛልና፥ ጠላቶቼንም ደስ አላሰኘህብኝምና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።
2አቤቱ አምላኬ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ ምሕረትም አደረግህልኝ።
3አቤቱ፥ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፥ ወደ ጕድጓድም እንዳልወርድ አዳንኸኝ።
4ቅዱሳን ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ።
5ቍጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፥ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን፤ ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል።
6እኔም በደስታዬ። ለዘላለም አልታወክም አልሁ።
7አቤቱ፥ በፈቃድህ ለሕይወቴ ኃይልን ሰጠሃት፤ ፊትህን መለስህ፥ እኔም ደነገጥሁ።
8አቤቱ፥ ወደ አንተ ጠራሁ፥ ወደ አምላኬም ለመንሁ።
9ወደ ጥፋት ብወርድ በደሜ ምን ጥቅም አለ? አፈር ያመሰግንሃልን? እውነትህንም ይናገራልን?
10እግዚአብሔር ሰማ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ረዳቴ ሆነኝ።
11ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ፥ ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ።
12አቤቱ አምላኬ፥ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።