ምዕራፍ 31
1አቤቱ አንተን ታመንሁ፤ ለዘላለም አልፈር፤ በጽድቅህም አድነኝ።
2ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ፤ ታድነኝ ዘንድ መታመኛ አምላክና የመጠጊያ ቤት ሁነኝ።
3አምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ መንገዴን አቅና ምራኝም።
4አንተ መታመኛዬ ነህና ከደበቁብኝ ወጥመድ አውጣኝ።
5በእጅህ ነፍሴን እሰጣለሁ፤ የእውነት አምላክ አቤቱ፥ ተቤዥተኸኛል።
6ከንቱ ምናምንቴነትን የጠበቁትን ጠላህ፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ።
7መከራዬን አይተሃልና፥ ነፍሴንም ከጭንቀት አድነሃታልና በምሕረትህ ደስ ይለኛል ሐሤትም አደርጋለሁ።
8በጠላቴ እጅ አልዘጋኸኝም፥ በሰፊም ስፍራ እግሮቼን አቆምህ።
9ተቸግሬአለሁና አቤቱ ምራኝ፤ ዓይኔም ከኃዘን የተነሣ ተፈጀች፥ ነፍሴም ሆዴም።
10ሕይወቴ በኅዘን አልቃለችና፥ ዓመታቴም በልቅሶ ጩኸት፤ ኃይሌ በችግር ደከመ፥ አጥንቶቼም ተነዋወጡ።
11በጠላቶቼ ዘንድ ተነወርኹ፥ ይልቁንም በጎረቤቶቼ ዘንድ፥ ለሚያውቁኝም ፍርሃት ሆንሁ፤ በሜዳ ያዩኝም ከእኔ ሸሹ።
12እንደ ሞተ ሰው ከልብ ተረሳሁ፥ እንደ ተበላሸ ዕቃም ሆንሁ።
13የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና፤ በዙሪያው ፍርሃት ነበረ፤ በላዬ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ነፍሴን ለመንጠቅ ተማከሩ።
14አቤቱ፥ እኔ ግን በአንተ ታመንሁ፤ አንተ አምላኬ ነህ አልሁ።
15ርስቴ በእጅህ ነው፤ ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ።
16ፊትህን በባሪያህ ላይ አብራ፥ ስለ ምሕረትህም አድነኝ።
17አቤቱ፥ አንተን ጠርቻለሁና አልፈር፤ ክፉዎች ይፈሩ በሲኦልም ዝም ይበሉ።
18በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ።
19በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፥ ቸርነትህ እንደ ምን በዛች!
20በፊትህ መጋረጃ ከሰው ክርክር ትጋርዳቸዋለህ፥ በድንኳንህም ከአንደበት ክርክር ትሸፍናቸዋለህ።
21በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን።
22እኔስ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፥ በድንጋጤ አልሁ፤ አንተ ግን ወደ አንተ በጮኽሁ ጊዜ የልመናዬን ቃል ሰማኸኝ።
23ሁላችሁ ቅዱሳኑ፥ እግዚአብሔርን ውደዱት፤ እግዚአብሔር እውነተኞችን ይፈልጋል፥ ትዕቢተኞችንም ፈጽሞ ይበቀላቸዋል።
24በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፥ በርቱ ልባችሁም ይጥና።