English

ምዕራፍ 32

1መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው።
2እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው።
3ሁልጊዜ ከመጮኼ የተነሣ ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤
4በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፥ እርጥበቴም ለበጋ ትኵሳት ተለወጠ።
5ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፥ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።
6ስለዚህ ቅዱስ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይለምናል፤ ብዙ የጥፋት ውኃም ወደ እርሱ አይቀርብም።
7አንተ ለእኔ መሸሸጊያዬ ነህ፥ ከጣርም ትጠብቀኛለህ፤ ከከበቡኝ ታድነኝ ዘንድ ደስታዬ ነህ።
8አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ።
9ወደ አንተ እንዳይቀርቡ በልባብና በልጓም ጉንጫቸውን እንደሚለጕሙአቸው፥ ልብ እንደሌላቸው እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ።
10በኃጢአተኛ ብዙ መቅሠፍት አለበት፤ በእግዚአብሔር የሚታመነውን ግን ምሕረት ይከብበዋል።
11ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ ሐሤትም አድርጉ፤ ልባችሁም የቀና ሁላችሁ፥ እልል በሉ።