ምዕራፍ 79
1አቤቱ፥ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ፤ የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ፥ ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት።
2የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ፥ የጻድቃንህንም ሥራ ለምድር አራዊት፤
3ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ፥ የሚቀብራቸውም አጡ።
4ለጎረቤቶቻችንም ስድብ ሆንን፥ በዙሪያችንም ላሉ ሣቅና ዘበት።
5አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘላለም ትቈጣለህ? ቅንዓትህም እንደ እሳት ይነድዳል?
6ስምህን በማይጠሩ መንግሥታት ላይ በማያውቁህም አሕዛብ ላይ መዓትህን አፍስስ፤
7ያዕቆብን በልተውታልና፥ ስፍራውንም ባድማ አድርገዋልና።
8የቀደመውን በደላችንን አታስብብን፥ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፥ እጅግ ተቸግረናልና።
9አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ እርዳን፤ ስለ ስምህ ክብር፥ አቤቱ፥ ታደገን፥ ስለ ስምህም ኃጢአታችንን አስተሰርይልን።
10አሕዛብ፥ አምላካቸው ወዴት ነው? እንዳይሉ፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ያወቁ፤
11የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን።
12አቤቱ፥ የተዘባበቱብህን መዘባበታቸውን ለጎረቤቶቻችን ሰባት እጥፍ በብብታቸው ክፈላቸው።
13እኛ ሕዝብህ ግን፥ የማሰማርያህም በጎች፥ ለዘላለም እናመሰግንሃለን፤ ለልጅ ልጅም ምስጋናህን እንናገራለን።