English

ምዕራፍ 21

1የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሾች በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ ወደ ወደደውም ያዘነብለዋል።
2የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኑ ፊት የቀናች ትመስለዋለች፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል።
3እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ጽድቅንና ቅን ነገርን ማድረግ ይወድዳል።
4ትዕቢተኛ ዓይንና ደፋር ልብ የኀጥኣንም እርሻ ኃጢአት ነው።
5የትጉህ አሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል፤ ችኵል ሰው ሁሉ ግን ለመጕደል ይቸኩላል።
6በሐሰተኛ ምላስ መዝገብ ማከማቸት የሚበንን ጉም ነው፤ ይህን የሚፈልጉ ሞትን ይፈልጋሉ።
7ቅን ነገርን ያደርጉ ዘንድ አይወድዱምና የኀጥኣን ንጥቂያ ራሳቸውን ያጠፋቸዋል።
8የበደለኛ መንገድ የጠመመች ናት፤ የንጹሕ ሥራ ግን የቀና ነው።
9ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በውጪ በቤት ማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል።
10የኀጥእ ነፍስ ክፉን ትመኛለች፥ በፊቱም ባልንጀራው ሞገስን አያገኝም።
11ፌዘኛ ቅጣትን በተቀበለ ጊዜ አላዋቂ ሰው ጥበብን ያገኛል፤ ጠቢብም ቢማር እውቀትን ይቀበላል።
12ጻድቅ ስለ ኀጥእ ቤት ያስባል፥ ኀጥኣንም ለጥፋት እንደ ተገለበጡ።
13የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም።
14ስጦታ በስውር ቍጣን ታጠፋለች፥ የብብትም ውስጥ ጉቦ ጽኑ ቍጣን ታበርዳለች።
15ፍርድን ማድረግ ለጻድቅ ደስታ ነው፤ ኃጢአትን ለሚያደርጉ ግን ጥፋት ነው።
16ከማስተዋል መንገድ የሚሳሳት ሰው በሙታን ጉባኤ ያርፋል።
17ተድላ የሚወድድ ድሀ ይሆናል፥ የወይን ጠጅንና ዘይትንም የሚወድድ ባለጠጋ አይሆንም።
18ኀጥእ የጻድቅ ቤዛ ነው፤ በደለኛም የቅን ሰው ቤዛ ነው።
19ከጠበኛና ከቍጡ ሴት ጋር ከመቀመጥ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል።
20የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል። አእምሮ የሌለው ሰው ግን ይውጠዋል።
21ጽድቅንና ምሕረትን የሚከተል ሕይወትንና ጽድቅን ክብርንም ያገኛል።
22ጠቢብ የኃያላንን ከተማ ይገባባታል፥ የሚታመኑበትንም ኃይል ያፈርሳል።
23አፉንና ምላሱን የሚጠብቅ ነፍሱን ከመከራ ይጠብቃል።
24ኵሩና ተጓዳጅ ሰው ፌዘኛ ይባላል፤ እርሱም በትዕቢት ቍጣ ያደርጋል።
25ታካችን ምኞቱ ትገድለዋለች፥ እጆቹ ይሠሩ ዘንድ አይፈቅዱምና።
26ኀጥእ ቀኑን ሁሉ ምኞትን ይመኛል፤ ጻድቅ ግን ይሰጣል፥ አይሰስትም።
27የኀጥኣን መሥዋዕት አስጸያፊ ነው፤ ይልቁንም በክፉ አሳብ ሲያቀርቡት አስጸያፊ ነው።
28ሐሰተኛ ምስክር ይጠፋል፤ የሚሰማ ሰው ግን ተጠንቅቆ ይናገራል።
29ኀጥእ ፊቱን ያጠነክራል፤ ቅን ሰው ግን መንገዱን ያጸናል።
30ጥበብ ወይም ማስተዋል ወይም ምክር በእግዚአብሔር ላይ የለም።
31ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ድል ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።